ሃውቲዎች በአሜሪካና ብሪታንያ የጦር መርከቦች ላይ ጥቃት ማድረሳችን ተጠናክሮ ይቀጥላል አሉ
የቡድኑ አዛዥ መሀመድ አል አቲፍ “አሜሪካና ብሪታንያን ለረጅም ጊዜ ለመዋጋት ዝግጁ ነን” ብለዋል
26 አባላት ያሉት የአውሮፓ ህብረት የራሱን የቀይ ባህር የቅኝት ቡድን ለማሰማራት ማቀዱን አስታውቋል
የየመኑ ታጣቂ ቡድን ሃውቲ በአሜሪካና ብሪታንያ የጦር መርከቦች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን መፈጸሙን እንደሚቀጥል አስታወቀ።
የቡድኑ ቃል አቀባይ ባወጡት መግለጫ፥ “የወራሪዎቹ አሜሪካና ብሪታንያ ሁሉም የጦር መርከቦች በኢላማችን ውስጥ ናቸው” ብለዋል።
በቀይ ባህር በሚጓዙና ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው ባላቸው እቃ ጫኝ መርከቦች ላይ ከህዳር 19 2023 ጀምሮ ጥቃቶችን በማድረስ ላይ የሚገኘው የሃውቲ ታጣቂ ቡድን የአሜሪካና ብሪታንያ የጦር መርከቦች ቀጣይ ኢላማዎቼ ናቸው ብሏል።
ትናንት ምሽትም ግራቨርሊ የተሰኘችው የአሜሪካ የጦር መርከብን ለመምታት ክሩዝ ሚሳኤል አስወንጭፎ እንደነበር ሬውተርስ ዘግቧል።
በመካከለኛው ምስራቅ የአሜሪካን ተልዕኮ የሚፈጽመው ማዕከላዊ እዝ ክሩዝ ሚሳኤሉን መትቶ ማጣሉን ማሳወቁ የሚታወስ ነው።
አብዛኛውን የየመን ክፍል የተቆጣጠረው ሃውቲ አዛዥ መሀመድ አል አቲፍ በየመን ተደጋጋሚ የአየር ድብደባ በመፈጸም ሉአላዊነታችን ጥስዋል ባሏቸው አሜሪካና ብሪታንያ የጦር መርከቦች ላይ ጥቃቱ እንደሚቀጥል ዝተዋል።
ቡድኑ ሁለቱን ሀገራት ለረጅም ጊዜ ለመዋጋት ዝግጁ መሆኑን መግለጻቸውም ተዘግቧል።
በኢራን ድጋፍ እንደሚደረግለት የሚታመነው የሃውቲ ታጣቂ ቡድን በዋሽንግተን እና ለንደን የአየር ድብደባዎች ጉዳት ማስተናገዱ ባይካድም እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመው ድብደባ እስካልቆመ ድረስ የቀይ ባህር ደህንነት አስጊ ሆኖ መቀጠሉን የሚያሳስብ መግለጫ አውጥቷል።
ቡድኑ የሀገራቱ ድብደባም ሆነ በሽብርተኝነት ዳግም መመዝገብ ለፍልስጤማውያን የሚያሳየውን አጋርነት እንደማይቀለብሰውም አመላክቷል።
ይህም የአለማችን ዋነኛ የሸቀጥ መተላለፊያውን መስመር ስጋት ውስጥ ጥሎ የአለም የሸቀጦች ዋጋ እየናረ እንዲሄድ እንደሚያደርግ ተንታኞች ያነሳሉ።
አሜሪካ መራሹን የቀይ ባህር ቅኝት ለመቀላቀል ፍላጎት ያልነበራቸው 26ቱ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራትም በየካቲት ወር አጋማሽ ወደ ቀጠናው የራሳቸው የቅኝት ቡድን ለማሰማራት ማቀዳቸው ተገልጿል።
በነገው እለት የህብረቱ ምክርቤት በብራሰልስ በሚያደርገው ምክክርም የትኛው ሃገር ተልዕኮውን እንደሚመራና መቀመጫው የት እንደሚሆን ይወስናል ነው የተባለው።
ኢራን በበኩሏ በቀይ ባህር የሚጓዙ መርከቦችን ደህንነት ለማስጠበቅ በሚል ምዕራባውያን የጦር መርከብና ወታደሮቻቸውን መላካቸው የጋዛውን ጦርነት አድማስ እያሰፋ የመካከለኛው ምስራቅ ውጥረትን እያባባሰው ይሄዳል ስትል አስጠንቅቃለች።