የየመኑ ሃውቲ የናስራላህ ግድያን ተከትሎ መሪዎቹን ወደ ሳዳ ዋሻ ማዛወሩ ተሰማ
ሃውቲ መሪዎቹ በእስራኤል የግድያ ኢላማ ውስጥ እንዳይገቡ በሰንአ የምድር ውስጥ መደበቂያ መገንባቱንም ምንጮች ለአል አይን ኒውስ ገልጸዋል
እስራኤል በሀምሌ ወር በሆዴይዳህ ወደብ ጥቃት ካደረሰች በኋላ የሃውቲ ዋና ዋና አመራሮች ከህዝብ እይታ እንዲሰወሩ ተደርጓል ተብሏል
የሄዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስራላህ በእስራኤል መገደል የየመኑ ሃውቲ ቡድን መሪዎቹን ለመጠበቅ የተጠናከረ እርምጃ እንዲወስድ አድርጎታል ተባለ።
የአል አይን ኒውስ ወታደራዊና የደህንነት ምንጮች እንደገለጹት፥ የየመኑ ቡድን ዋና ዋና መሪዎቹ በእስራኤል የግድያ ኢላማ ውስጥ እንዳይገቡ ሙሉ በሙሉ ከህዝብ እይታ እንዲሰወሩ አድርጓል።
ሃውቲዎች የሄዝቦላህ እና ኢራን አማካሪ ባለሙያዎችን ለደህንነታቸው የተሻለ ነው ወደተባለው የሳዳ ዋሻ ማዛወራቸውንም ነው ምንጮቹ ያነሱት።
ቡድኑ በሳዳ አስቀድሞ ተዘጋጅቶበት ለስራ አመቺ አድርጎ የሰራው ዋሻ ወታደራዊ ቁሳቁሶች የተሟሉለትና የአደጋ ጊዜ ወታደራዊ ማዛዣ ሆኖ ሲያገለግል መቆየቱም ተገልጿል።
አካባቢው በበርካታ ተራራዎች የተከበበ መሆኑም በእስራኤል የአየር ጥቃት ኢላማ የመደረግ እድሉን ያጠበዋል ተብሎ ታምኖበታል።
በአሜሪካ መረጃ አቀባይነት የሃውቲ መሪዎች እንዳይገደሉ በሚልም ቡድኑ በአለማቀፍ ድርጅት ተቀጥረው በመስራት ለዋሽንግተን ሲሰልሉ ነበሩ የተባሉ የቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች ቤተሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉም ተሰምቷል።
የየመኑ ቡድን በሰንአ የሚንቀሳቀሱ የአለማቀፍ ተቋማት ዋነኛ ስራ ለተራቡ የመናውያን መድረስ ሳይሆን የስለላ መረጃን ለአሜሪካ እና እስራኤል ማቀበል ነው ብሎ ያምናል።
እስራኤል በሀምሌ ወር በሆዴይዳህ ወደብ ጥቃት ካደረሰች በኋላ የሃውቲ ዋና ዋና አመራሮች ከተዘጋጀላቸው ማረፊያ ወጥተው ከህዝብ ጋር እንዳይገናኙ መደረጉን የአል አይን ኒውስ ምንጮች ተናግረዋል።
ቡድኑ መሪዎቹን ከእስራኤል ጥቃት የሚጠብቅ የደህንነት ክፍል አዋቅሮ የማይጣሱ ጥብቅ ትዕዛዞች ማስተላለፉንም አብራርተዋል።
የአል አይን ኒውስ ምንጮች የየመኑ ሃውቲ በመዲናዋ ሰንአ ለአደጋ ጊዜ መደበቂያ የሚሆኑ ዋሻዎች መገንባታቸውንና የቡድኑ ከፍተኛ አመራሮችም ከሀምሌ ወር ጀምሮ በነዚህ ዋሻዎች ውስጥ እንዲገቡ መደረጉን ነው ያነሱት።
እስራኤል ከትናንት በስቲያ በምዕራባዊ የመን ሆዴይዳህ ወደብ ከፍተኛ ፍንዳታ ያስከተለ ጥቃት መፈጸሟ ይታወሳል።
የሆዴይዳሁ ጥቃት ሃውቲዎች በቴል አቪቭ ወደሚገኘው የቤን ጉሪን አውሮፕላን ማረፊያ ላስወነጨፉት የባለስቲክ ሚሳኤል አጻፋ ነበር።
እስራኤልና ሃማስ ባለፈው አመት ጥቅምት ወር ጦርነት ከጀመሩ ወዲህ የየመኑ ቡድን ለፍልስጤማውያን አጋርነቱን በማሳየት በእስራኤል ላይ ጥቃት ሲያደርስ ቆይቷል።
ከቴል አቪቭ እና ዋነኛ አጋሯ ዋሽንግተን ጋር ግንኙነት አላቸው ባላቸውና በቀይ ባህር በሚጓዙ መርከቦች ላይም የሚሳኤልና የድሮን ጥቃት መፈጸሙ ይታወቃል።