የየመኑ ሃውቲ ከራዳር እይታ በሚሰወር ድሮን ቴል አቪቭ ላይ ጥቃት ማድረሱን ገለጸ
እስራኤል የአንድ ግለሰብን ህይወትን የቀጠፈውና በርካቶች ላይ ጉዳት ያደረሰውን ጥቃት እየመረመርኩ ነው ብላለች
የእስራኤል ጦር የሄዝቦላህ ከፍተኛ አመራርን መግደሉን ካረጋገጠጠ ከስአታት በኋላ ነው በቴል አቪቭ የድሮን ጥቃት የተፈጸመው
የእስራኤል ጦር በማዕከላዊ ቴል አቪቭ ዛሬ ጠዋት የደረሰው ጥቃት በድሮን ሳይፈጸም እንደማይቀር ገለጸ።
ጦሩ በጥቃቱ ዙሪያ ዝርዝር ምርመራ እየተደረገ ነው ያለ ሲሆን፥ የሀገሪቱ የአየር መቃወሚያ ስርአትም እንዲጠናከር አዟል።
የሀገሪቱ ፖሊስ በጥቃቱ ህይወቱ ያለፈ የአንድ ግለሰብን አስከሬን ፍንዳታው ከተከሰተበት አካባቢ ማግኘቱን አስታውቋል። በርካታ ሰዎች ላይም ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን ነው የገለጸው።
የሃማስ፣ ሄዝቦላህ እና ሃውቲ የሚሳኤል እና ሮኬት ጥቃቶችን አየር ላይ የሚያመክነውና የእስራኤል ጋሻ የሚባለው “አይረን ዶም” ዛሬ ጠዋት ወደ መዲናዋ የገባውን ድሮን መምታት አለመቻሉ ጥያቄ አስነስቷል።
የእስራኤል ጦር የሄዝቦላህ ከፍተኛ አመራሩን ሃቢብ ማቱክ መግደሉን ካረጋገጠጠ ከስአታት በኋላ ነው በቴል አቪቭ ጥቃት የደረሰው።
የሊባኖሱ ቡድን ከዚህ ጥቃት ጋር በተያያዘ እስካሁን መግለጫ አላወጣም።
እንደ ሄዝቦላህ ሁሉ ከቴህራን የገንዘብና ጦር መሳሪያ ድጋፍ ያገኛል የሚባለው የሃውቲ ታጣቂ ቡድን ግን “ቴል አቪቭ ላይ ላነጣጠረው ወታደራዊ ዘመቻ” ሃላፊነቱን እንደሚወስድ ገልጿል።
ጥቃቱን የፈጸመበት አዲስ ድሮን ከራዳር እይታ ውጭ ሆኖ በመጓዝ ኢላማውን መምታት እንደሚችልም ነው የቡድኑ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ የተናገሩት።
አዲሱ ድሮን የአሁኗ እስራኤል በተመሰረተችበት የቀድሞዋ የፍልስጤም የወደብ ከተማዋ “ጃፋ” መሰየሙንም በመጥቀስ።
ለሃማስ አጋርነታቸውን ያሳዩት የሃውቲ እና ሄዝቦላህ ቡድኖች እስራኤል ፍልስጤማውያን መጨፍጨፏንና ጋዛን ማውደሟን ካላቆመች ጥቃታቸው እንደማይቆም ደጋግመው መግለጻቸው ይታወሳል።
በሊባኖስ ድንበር ያለው የተኩስ ልውውጥ እየተባባሰ መሄዱም አዲስ የጦርነት ሜዳ ይከፍታል የሚለውን ስጋት እያናረው ይገኛል።