አሜሪካ በሃውቲ ታጣቂዎች ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ እንደምትጀምር አስጠነቀቀች
በቀይ ባህር ቅኝት እያደረገ የሚገኘው አሜሪካ መራሹ የጋራ ግብረሃይል ለየመኑ ቡድን የመጨረሻ ያለውን ማስጠንቀቂያ አስተላልፏል
የሃውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር በሚጓዙ መርከቦች በጥቂቱ 23 ጥቃቶችን ፈጽመዋል ተብሏል
አሜሪካ በሃውቲ ታጣቂዎች ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ እንደምትጀምር አስጠነቀቀች።
በቀይ ባህር የሃውቲዎችን ጥቃት ለማስቆም የተቋቋመው የጋራ የባህር ቅኝት ግብረሃል ለየመኑ ቡድን የመጨረሻ ነው ያለውን ማስጠንቀቂያ አስተላልፏል።
በዚህ የማስጠንቀቂያ መልዕክት ላይ አሜሪካ፣ አውስትራሊያ፣ ባህሬን፣ ቤልጂየም፣ ካናዳ፣ ዴንማርክ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓን፣ ኔዘርላንድስ፣ ኒውዝላንድ፣ ሲንጋፖርና ብሪታንያ ፊርማቸውን አኑረዋል።
ሀገራቱ የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት በሃውቲ ታጣቂዎች እና የፋይናንስ ድጋፍ በምታደርግላቸው ኢራን ላይ እርምጃ እንዲወስድም ጠይቀዋል ብሏል አሶኤትድ ፕረስ በዘገባው።
ቡድኑ የሚፈጽመውን ህገወጥ ተግባር እንዲያቆምና በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን መርከቦች እንዲለቅ የጠየቁት ሀገራቱ፥ በቀይ ባህር ደህንነት መናጋት ምክንያት በአለም ምጣኔ ሃብት ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ቡድኑ ሃላፊነቱን ይወስዳል ሲሉም ገልጸዋል።
ስማቸውን ያልጠቀሱ የባይደን አስተዳደር ከፍተኛ ባለስልጣንም “በኢራን የሚደገፉት የሃውቲ ታጣቂዎች ከዚህ በኋላ ከአሜሪካና አጋሮቿ የማስጠንቀቂያ መልዕክት አይጠብቁ” ያሉ ሲሆን ቡድኑ ጥቃቱን ከቀጠለ ወታደራዊ እርምጃ ልንወስድ እንችላለን ብለዋል።
የአሜሪካው ባለስልጣን በየመኑ ቡድን ላይ ሊወሰድ ስለሚችለው ወታደራዊ እርምጃ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥበዋል።
እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የምትፈጽመውን በደል ካላቆመች ጥቃቴ ይቀጥላል ያለው የሃውቲ ታጣቂ ቡድን ትናንት ያወጣው መግለጫ ግን ለሀገራቱ ማስጠንቀቂያ ቁብ አልሰጠውም።
ቡድኑ ከታህሳስ 19 2023 ወዲህ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው ባላቸው መርከቦች ላይ በጥቂቱ 23 ጥቃቶችን መፈጸሙ ተነግሯል።
ባለፈው ሳምንትም የሲንጋፖር ሰንደቅ የምታውለበልብ መርከብን ለማገት ሙከራ ሲያደርግ የአሜሪካ ሄሊኮፕተሮች ሶስት የቡድኑን ጀልባዎች ማስመጡና 10 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።
ሃውቲ በአሜሪካ የተፈጸመውን ጥቃት እንደሚበቀል መዛቱና በመርከቦች ላይ ያነጣጠሩት የጥቃት እርምጃዎች የጋዛው ጦርነት እስካልቆመ ድረስ ይቀጥላል ማለቱም ውጥረቱን እንዳናረው ነው።
አሜሪካና አስተባብራ ያሰለፈቻቸው 12 ሀገራት በቀጣይ ወታደራዊ እርምጃ የሚወስዱ ከሆነም ከጋዛ ተነስቶ ቤሩት የደረሰው ጦርነት ሰንአ መግባቱ የሚቀር አይመስልም።