የሀውቲ ታጣቂዎች የአሜሪካ ሰንደቅአላማ ስታውለበልብ የነበረችን መርከብ ማጥቃታቸውን አስታወቁ
አሜሪካ እና እንግሊዝ የመን ውስጥ በሀውቲ ታጣቂዎች ይዞታዎች ላይ የአየር ድብደባ እየፈጸሙ ናቸው
የየመን ሀውቲ ታጣቂዎች በኤደን ባህረ ሰላጤ ቶርም ቶር በተባለች ነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን አስታወቀዋል
የሀውቲ ታጣቂዎች የአሜሪካ ሰንደቅአላማ ስታውለበልብ የነበረችን መርከብ ማጥቃታቸውን አስታወቁ
የየመን ሀውቲ ታጣቂዎች በኤደን ባህረ ሰላጤ ቶርም ቶር በተባለች ነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን አስታወቀዋል።
ታጣቂዎቹ የአሜሪካ ሰንደቅአላማ የምታውለበልብ እና ንብረትነቷም የአሜሪካ የሆነችውን ቶርም ቶር ነዳጅ ጫኝ መርከብ ማጥቃታቸውን የታጣቂዎቹ ቃል አቀባይ ያህያ ሰሪኣ በዛሬው እለት ተናግሯል።
ይህ ጥቃት ታጣቂዎቹ ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ላለው የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ አጋርነት ለማሳየት የሚያደርጉት ዘመቻ አካል ነው።
ሰሪኣ በቴሌቪዥን በተላለፈ መልእክቱ እንደገለጸው ታጣቂዎቹ በበርካታ የናቫል ሚሳይሎች በመርከቧ ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል።
የአሜሪካ ማዕከላዊ ኮማንድ(ሴንትኮም) እንደገለጸው የአሜሪካ ተልዕኮ መርከቧን ሊመታ የሚችል ከሀውቲ ታጣቂዎች የተወነጨፈ ጸረ-መርከብ ሚሳይል መትቶ ጥሏል።
ሴንትኮም ባወጣው መግለጫ የአሜሪካ ተልእኮም ሆነ ቶርም ቶር የደረሰባት ጉዳት የለም ብሏል።
እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ጥቃት የሚቃወሙት ታጣቂዎቹ ከህዳር ወር ጀምሮ በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ በሚጓዙ መርከቦች ላይ ጥቃት እየሰነዘሩ ይገኛሉ።
አሜሪካ እና እንግሊዝ የመን ውስጥ በሀውቲ ታጣቂዎች ይዞታዎች ላይ የአየር ድብደባ እየፈጸሙ ነው፣ ታጣቂዎቹንም በድጋሚ በሽብርተኝነት ፈርጀዋቸዋል።
በእስራኤል እና በሀማስ መካከል ያለው ግጭት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ወደ መካከለኛው ምስራቅ ተስፋፍቷል።
ሀውቲዎች ወሳኝ በሚባለው የመርከብ መስመር ላይ ከሚያደርሱት ጥቃት በተጨማሪ፣ የሊባኖሱ ሄዝቦላ ከእስራኤል ጋር ድንበር ላይ ግጭት ውስጥ የገባ ሲሆን በኢራቅ የሚገኙት እና በኢራን የሚደረገፉት ታጣቂዎች በመካከለኛው ምስራቅ በሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈሮች ላይ ጥቃት እያደረሱ ነው።