አዲሱ የሩሲያ እና አሜሪካ የሚሳይል ፉክክር ምን ያህል አደገኛ ነው?
ሩሲያ ማምረት አቁማው የነበረውን አህጉር አቋራጭ የረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳይል ምርት ድጋሚ እንደምትጀምር ዝታለች
የረጅም ርቀት ሚሳይሎቹ ሚሳኤሎች ከ500 እስከ 5 ሺህ ኪሎሜትር መምዘግዘግ የሚችሉ ናቸው
አዲሱ የሩሲያ እና አሜሪካ የሚሳይል ፉክክር ምን ያህል አደገኛ ነው?
አሜሪካ እና ሩሲያ አዲስ የጀመሩት የሚሳይል ፉክክር በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ደህንነት ላይ ከፍተኛ ስጋት መደቀኑ ተነገረ፡፡
በዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ምክንያት እየተካረረ የመጣው የዋሽንግተን እና ሞስኮ ግንኙነት ወደ ቀደመው የጦር መሳሪያ እሽቅድድም እየተንደረደረ ነው።
ከአራት አስርተ አመታት በፊት አሜሪካ የሶቭየት ህበረትን የኤስኤስ-20 የረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳይሎችን ጥቃት ለመመከት ኒውክሌር አረር ተሸካሚ ሚሳኤሎችን በአውሮፓ ሀገራት አሰማርታ ነበር ፡፡
በ1987 በቀድሞው ሶቭየት ህብረት መሪ ሚካኤል ጎርባቾቭ እና በአሜሪካው ፕሬዝዳነት ሮናልድ ሬገን መካከል በተደረሰ ስምንት ሁለቱ ሀገራት ከ500 እስከ 5 ሺህ ኪሎሜትር የሚምዘገዘጉ የመካከለኛ እና ረጂም ርቀት ሚሳይሎችን ምርት ለመቀነስ እና ለመቆጣጠር እንዲሁም ተተክለው የነበሩትን ሚሳይሎች ለማንሳት ተፈራርመዋል፡፡
ይህ ስምምነት እሰከ 2019 ድረስ መዝለቅ የቻለ ሲሆን ይህን ተከትሎ ሁለቱም ሀገራት እነዚህን ሚሳይሎች ድጋሚ ጥቅም ላይ ለማዋል እና የምርት መጠናቸውን ለመጨመር በየራሳቸው ሲዘጋጁ ሰንብተዋል፡፡
ባሳለፍነው ወር መጨረሻ ላይ ደግሞ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሞስኮ ከዋሽንግተን ጋር በገባቸው ስምምነት መሰረት አቁማቸው የነበሩትን አህጉር አቋራጭ ሚሳኤሎችን ምርት ዳግም እንደሚያስጀምሩ በይፋ ተናግረዋል፡፡
አሜሪካ በበኩሏ በባለፈው ሰምንት ከተካሄደው የኔቶ አመታዊ ጉባኤ መጠናቀቅ በኋላ እስከ 2026 በጀርመን የኤስ-6 ሀይፐር ሶኒክ እና ቶም ሃውክስ የተሰኙ የረጅም ርቀት ሚሰኤሎችን እንደምታሰፍር ይፋ አድርጋለች፡፡
በዚህ የተነሳም ሁለቱ ተፎካካሪ ሀገራት በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት እንደነበሩበት አይነት የጦር መሳሪያ እሽቅድድም ሽኩቻ ውስጥ መግባታቸው ለአለም አቀፉ ማህበረሰቡ ተጨማሪ ስጋትን ደቅኗል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመሳርያ ቁጥጥር ኢንስቲቲዩት ተመራማሪ አንድሪው ባክሊቲስኪ እንደሚሉት በአሜሪካ እና ሩስያ መካከል እንደ አዲስ የተቀሰቀሰው የሚሳኤል ፉክክር እና ሚሳይሎቹ የሚሰፍሩባቸው አካባቢዎች በሀገራቱ መካከል ቀጥተኛ ወታደራዊ ግጭትን የመቀስቀስ እድሉን የሚያሰፋ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ተመራራማሪው የቢሆን ግምታቸውን ሲያስቀምጡ ፉክክራቸው እየበረታ ከሄደ ሩሲያ በዩክሬን የሚገኝውን የምዕራባውን የጦር መሳሪያ ማከማቻ ዲፖ ልትመታ ትችላለች፤ አሜሪካም አጸፋውን ለመመለስ በሩሲያ የራዳር ቁጥጥር ቅኝት እና ማዘዣ ማዕከላት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ልትፈጽም ትችላለች ብለዋል፡፡
ሁለቱም ሀገራት አሁን በሚገኙበት ወታደራዊ አቅም ጥቃቱን በባህር አልያም በአየር ሊፈጽሙት ይችላሉ ያሉት ተመራማሪው፤ አሜሪካ በጀርመን ለመትከል ያቀደቻቸው ሚሳኤሎች ለምዕራባውያን አጋሮቿ ደህንነት ማስተማመኛ ከመስጠት ባለፈ ከሞስኮ ጋር የሚገኙበትን የተካረረ ውጥረት የሚያሳይ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባለፈ የሩቅ ምስራቋ ቻይና በዚህ ውስጥ የሩሲያ አጋር ሆና የምትቆምበት እድል ሰፊ ነው፡፡
የአሜሪካ መከላከያ ሚንስቴር በ2023 ለኮንግረሱ ባቀረበው ሪፖርት ቻይና ከ300 እስከ እስከ 3ሺህ ኪሎ ሜትር መጓዝ የሚችሉ 2300 ሚሳይሎች እስከ 5ሺህ 500 መቶ ኪሎ ሜትር የሚጓዙ ደግሞ 500 ሚሳኤሎች እንዳሏት ተናግሯል፡፡
እነዚህ ሚሳይሎች ሞስኮ እና ቤጂንግ በቀጣይ በሚያደርጓቸው ወታደራዊ ልምምዶች ላይ ለማካተት መስማማታቸው ደግሞ የተፈራው 3ተኛው የአለም ጦርነት መቀስቀስ ምክንያት እንዳይሆን አስግቷል፡፡