የአሜሪካና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሳኡዲ ውይይት አድርገዋል
አሜሪካ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ያለው ውጥረት እንዲረግብ ጠየቀች።
የአሜሪካና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሳኡዲ እየተካሄደ ካለው አይ ኤስን ለመዋጋት የተቋቋመው ዓለም አቀፍ ጥምረት የሚኒስትሮች ጉባዔ ጎን ለጎን ውይይት አድርገዋል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በዚሁ ወቅት፥ “ግጭት የማቆም ስምምነቱ አፈጻጸም ሂደት አስደንቆናል” ብለዋል።
- የምርጫ ቦርድ ውሳኔ "የሰላም ስምምነቱን የሚፈታተን" ነው ሲል የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ተቃወመ
- በትግራይ ክልል የተለያዩ ጥያቄዎች የተስተናገዱበት ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄደ
የሰላም ስምምነቱ ትግበራ በትግራይ ክልል የነበረውን ሁኔታ በእጅጉ እንደቀየረውም ነው የተናገሩት።
አሜሪካ ሰላሙን ዘላቂ በሚያደርጉና ሌሎች ጉዳዮች ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነቷን ይበልጥ ማሳደግ እንደምትፈልግም አብራርተዋል።
ከሰላም ስምምነቱ ባሻገር በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያለውን ውጥረት ማርገብ፣ የሽግግር ፍትህ ማስፈን እና የእርዳታ እህልን ለሚገባው አካል ማድረስ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ምክክር መደረጉንም ብሊንከን በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮነን በበኩላቸው፥ ከስምምነቱ በኋላ አበረታች ለውጦች መታየታቸውን ነው ያነሱት።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከፌደራል መንግስት ጋር ተቀራርቦ መስራት መጀመሩንና የተሃድሶ ኮሚሽን ተቋቁሞ የተለያዩ ስራዎች መቀጠላቸውን ተናግረዋል።
የሰላም ሂደቱ ውጤታማ እየሆነ እንዲሄድም ተከታታይ ምክክሮች እንደሚደረጉ ነው ለሚኒስትሩ የነገሯቸው።
የአሜሪካ እና ኢትዮጵያ የረጅም አመታት ግንኙነት በሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ሻክሮ መቆየቱ አይዘነጋም።
በፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ግን ሀገራቱ ግንኙነታቸውን ማደስ ጀምረዋል።
ብሊንከን በመጋቢት ወር 2015 በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ማድረጋቸውም የዚሁ ማሳያ ተደርጎ ይጠቀሳል።