የአውሮፓ ህብረት “ሩሲያ የእህል ምርት ወደ ውጭ እንዳይወጣ መከልከሏ የጦር ወንጀል ነው” አለ
ሩሲያ በድርጊቱ የምትቀጥልበት ከሆነ “ተጠያቂ መሆን አለባት” ሲልም ህብረቱ አሳስቧል
የአውሮፓ ህብረት ሩሲያ ምግብን እንደ “ድብቅ ሚሳዔል” እየተጠቀመች ነው የሚል ክስ ሲያቀርበ እንደነበር አይዘነጋም
ሩሲያ የምግብ እህሎች ለዓለም ገበያ እንዳይላክ መከልከሏ “እውነተኛ የጦር ወንጀል ነው” ሲሉ የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ ተናገሩ።
የአውሮፓ ህብረት ሩሲያ የምግብ አቅርቦትን እንደ ድብቅ ሚሳዔል እየተጠቀመች ነው በሚል በተለያዩ ጊዜያት ሲከስ መቆየቱ ይታወሳል።
በዚህም መሰረት በአውሮፓ የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትሮች ስብሰባ ላይ የጉዳዩን አሳሳቢነት ያነሱት የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካዩ ጆሴፕ ቦረል፤ ሩሲያ በጣም አስፈላጊ የሆነውን እህል ከዩክሬን ወደ ውጭ እንዳይላክ ማድረጓን የምትቀጥል ከሆነ “ተጠያቂ መሆን አለባት” ማለታቸውን ዘ-ቴሌግራፍ ዘግቧል።
በሌሎች የዓለም ክፍሎች ላይ ሰዎች በረሃብ እየተሰቃዩ ባለበት ወቅት፤ በሚሊየን የሚቆጠሩ ቶን ስንዴዎች በዩክሬን ውስጥ ተዘግተው እንደሚቆዩ ማሰብ እጅግ ከባድ ነው ያሉት ቦሬል ድርጊቱ " የጦር ወንጀል ነው” ብለዋል።
"ሩሲያ፡ የዩክሬን ወደቦችን ክፍት እንድታደርግ እንጠይቃለን" ሲሉም አክለዋል ከፍተኛ ተወካዩ።
ሩሲያ የምግብ አቅርቦትን እንደ ‘ድብቅ ሚሳኤል’ እየተጠቀመችበት ነው፤ ሲሉ አውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቻርለስ ሚሸል በቅረቡ በኒውዮርክ በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ መናገራቸው ይታወሳል።
ሚሸል “የሚያሳዝነው ሩሲያ የጀመረችው ጦርነት በመላው ዓለም እየተዛመተ መሆኑ ነው፤ የምግብ ዋጋ እጅጉን እንዲንር በማድረግ የዓለም ህዝቦች ለድህነት እንዲዳረጉና የተለያዩ ቀጠናዎች እንዲታመሱ እያደረገ ነው ፤ለዚህ ሁሉ ቀውስ ተጠያቂ ሩሲያ መሆኗ ሊታወቅ ይገባል” ነበር ያሉት በወቅቱ ባደረጉት ንግግር።