የአውሮፓ ህብረት የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር በመቀሌ እና አዲስ አበባ ስለነበራቸው ቆይታ ምን አሉ?
ኮሚሽነሩ “የትግራይ ተወላጆች በቂ ስቃይ ደርሶባቸዋል፤ መሰረታዊ አገልግሎቶች መመለስ አለባቸው” ሲሉ አሳስበዋል
አውሮፓ ህብረት “በጣም ተጋላጭ የሆኑትን ዜጎች ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ለአቶ ደመቀ አረጋግጬላቸዋለሁ”ም ብለዋል ኮሚሽነሩ
በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ከተከሰተ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ትግራይን የጎበኙት የአውሮፓ ህብረት የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ዣኔዝ ሌናርቺች በትግራይ ቆይታቸው ስለተመለከቷቸው አሳዛኝ እና ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽነሩ በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ወደ ትግራይ በሚገቡ የሰብአዊ ርዳታ አቅርቦት መሻሽሎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡በአብዛኛው ምግብ የያዙ መኪኖች መቀሌ እየደረሱ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ አሁን የሚታየው ለውጥ የበለጠ ማደግ አለበትም ብለዋል፡፡
የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞች ለተቸገሩት ሁሉ እርዳታ እንዲያደርሱ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች በአስቸኳይ መሻሻል አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል ኮሚሽነሩ፡፡
“የትግራይ ተወላጆች በቂ ስቃይ ደርሶባቸዋል፤ስለዚህም ለህዝቡ መሰረታዊ አገልግሎቶች መመለስ አለባቸው” ሲሉም አክለዋል፡፡
ኮሚሽነሩ በትግራይ ቆይታቸው መሬት ላይ ያለውን እውነታን መስማት በተለይም የትግራይ ተወላጆች እያጋጠሟቸው ስላለው አስከፊ ሰብአዊ ችግር ማወቅ አስፈላጊ ስለነበር፤ የክልሉ ባለስልጣት ማነጋገረቸውም ገልጸዋል፡፡
“በመቀሌ በነበርኩበት ወቅት የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደብረፂዮን ገብረሚካኤልን (ዶ/ር) አግኝቻለሁ” ያሉት ኮሚሽነሩ፤ አንዳንድ መሰረታዊ የህይወት አድን እርዳታዎችን በበለጠ ለማስገባት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተናል ብለዋል፡፡
ለግጭቱ ዘለቂ መፍትሄ እንዲመጣ የትግራይ ባለስልጣናት “ያልተቋረጠ የሰብአዊ አቅርቦት እንዲኖር የወሰዱት እርምጃ እንዲቀጥሉበት አሳስቤያለሁ”ም ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፡፡
በተፋላሚ ወገኖች መካከል የተፈጠረውን መሻሻል በደስታ እቀበላለሁም ብለዋል ኮሚሽነሩ፡፡
ኮሚሽነር ዣኔዝ ሌናርቺች በኃይል አቅርቦትና ከፍተኛ የመድሃኒት እጥረት ምክንያት ስራው እንዳቆመ የሚነገርለት የዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል መጎብኘታቸውም አስታውቀዋል፡፡
በሆስፒታሉ ስለተመለከቱት አጠቃላይ ሁኔታ ሲናገሩም “በዓይደር ሆስፒታል ያሉት የህክምና ባለሙያቹ የስራ ተነሳሽነት አስደስቶኛል”ብለዋል፡፡
ይሁን እንጅ፤ ነገሮች ቢስተካከሉ እዚህ መሆን አይገባቸውም ነበር ስላልዋቸውና በሆስፒታሉ በህመም ሲሰቃዩ በተመለከትዋቸው ህጻናት ማዘናቸው አልሸሸጉም ኮሚሽነሩ፡፡“በዓይደር ሆስፒታል ያየኋቸው ህጻናት አሳዝነውኛል”ም ነበር ያሉት፡፡
ኮሚሽነሩ ወደ ትግራይ ከማቅናታቸው በፊት ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አቶ ደመቀ ጋር መወያየታቸውም አንስተዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ከአቶ ደመቀ መኮንን ጋር በነበራቸው ቆይታ “በኢትዮጵያ ሰብዓዊ ድጋፍ ዙርያ ያሉ ሁኔታዎችን” ትኩረት አድርገው መወያየታቸው ገልጸዋል ፡፡
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ወደ 30 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎቿ ሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ከአቶ ደመቀ መኮንን በነበራቸው ውይይት ማንሳታቸውን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ አውሮፓ ህበረት “በጣም ተጋላጭ የሆኑትን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ለምክትል ጠቅላይ ሚኒሰትሩ አረጋግጬላቸዋለሁ”ም ብለዋል።
የዓለም ትኩረት በዩክሬን ባለው ቀውስ ቢሆንም የአውሮፓ ህብረት በሌላው ዓለም ያለውን ቀውስ እንዳልዘነጋው ማስረዳታቸውም ጭምር ተናግረዋል፡፡
“የእኛ(አውሮፓ ህብረት) የህይወት አድን እርዳታ በመላ ሀገሪቱ በጣም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖቻችን እንዲደርስ፣ ኢትዮጵያ የተቻላትን ሁሉ እንድታደርግ አሳስቤያለሁ” ሲሉም አክለዋል።