ተመድ “በትግራይ ያለው የመጠለያ አቅርቦት እጥረት”ያሳስበኛል አለ
በትግራይ በትምህርት ቤቶች ውስጥ 40 እና 50 የሚሆኑ ተፈናቃዮች በአንድ ክፍል ተጠልለው ይገኛሉ ብሏል ተመድ
በትግራይ የመጠለያ ጣብያዎች ለመገንባት የሚያስችሉ ተጨማሪ ቦታዎች እንደሚያስፈልጉ የተመድ የስደተኞች ኮሚሽን ገልጿል
በትግራይ የመጠለያ አቅርቦት እጥረት መኖሩ እጅጉን እንደሚያስስበው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ገለጸ፡፡
በትግራይ ክልል ከስድስት ወራት በፊት ያገጠመውን ግጭት ተከትሎ ከ 1.7 ሚልዮን በላይ ተፈናቅለው በመቀሌ፣ሽረ እና ዓድግራት በመሳሰሉ ከተሞች እንዲሁም የተለያዩ የጋራ መኖርያና ትምህርት ቤቶች ተጠለው እንደሚገኙ የተመድ መረጃ ያመላክታል፡፡
የተመድ የስደቶኞች ኤጀንሲ /ዩኤን.ኤች.ሲአር/ በትግራይ የተፈናቀሉ ዜጎች ያሉበት ሁኔታና ያለው የመጠለያ አቅርቦት ተመጣጣኝ ባለመሆኑ እጅጉን ያሳስበኛል ብሏል፡፡
በኢትዮጵ የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ /ዩኤን.ኤች.ሲአር/ ቃል አቀባይ ኤሊዛቤት አርንስዶርፍ የትግራይ ተፈናቃዮች ሁኔታን በተመለከተ ከአል-ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
ኤሊዛቤት አርንስዶርፍ በቅርቡ ወደ ትግራይ አቅንተው የተመለከቱት እና የታዘቡት የስደተኞች ሁኔታም ለአል-ዐይን አጋርቷል፡፡
“ባለፉት ቀናት መቀለ ነበርኩኝ፤ በትምህርት ቤቶች ውስጥ 40 እና 50 የሚሆኑ ተፈናቃዮች በአንድ ክፍል ተጠለው ይገኛሉ፤ ይህ ካለው የኮሮና ወረርሺኝ አንፃር አደጋ አለው፤ ለተላላፊ በሽታዎችም ጭምር የሚያጋልጥ ነው፤ ለሴቶች እና ልጃገረዶች ደህንነትም እንዲሁ ስጋት ነው” ሲሉም ነበር ትዝብታቸውን ያጋሩት ቃል አቀባይዋ ኤሊዛቤት አርንስዶርፍ፡፡
ለተፈናቃዮች የሚደረገውን እርዳታ በተመለከተ የስደተኞች ኤጀንሲው/ዩኤን.ኤች.ሲአር/ ተደራሽ ያልሆኑ ስደተኞችን ለመርዳት ተደራሽነቱን ለማሳደግ እየሰራ ቢሆንም በክልሉ ካለው ተለዋዋጭ ሁኔታ ጋር ተያይዞ በሚፈለገው ልክ እንዳልሆነ አንስተዋል፡፡ ኤጀንሲው እርዳታን በሚፈለገው መጠን ለማዳረስ አሁንም ያልተገደበ መዳረሻ እንደሚያስፈልገው በመጠቆም፡፡
የተመድ ስደተኞች ኤጀንሲ/ዩኤን.ኤች.ሲአር/ ለትግራይ ተፈናቃዮች አዳዲስ መጠለያ ጣብያዎች እየገነባ ቢሆነም ፤ ያለው ከፍተኛ የተፈናቃች ቁጥር ሁኔታውን ከባድ አድርጎታልም ብለዋል ቃል አቀባይዋ፡፡
ኤሊዛቤት አርንስዶርፍ “አዳዲስ መጠለያ ጣብያዎች እየገነባን ቢሆንም አቅርቦቱ አሁንም ካለው ፍላጎት ጋር የተመጣጠነ አይደለም፤ ምክንያቱም እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ህፃናት፣ሴቶች እና ወንዶች ናቸው የተፈናቀሉት፤ ይህ የክረምት ዝናብ ወቅት እየቀረበ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ለኛ እጅጉን የሚያሳስብ ጉዳይ ነው” በማለትም የትግራይ ተፈናቃዮች ሁኔታ ገልፀውታል፡፡
ካለው የተፈናቀዮች ቁጥር ጋር በተያያዘ ተጨማሪ የመጠለያ ጣብያዎች ለመገንባት የሚያስችሉ ቦታዎች እንደሚያስፈልግ ቃል አቀባይዋ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የትግራይ ክልልን ሰብአዊ እርዳታ ለሚያደርጉ አለምቀቀፍ ድርጅቶችና ለሚዲያ ክፍት ማድረጉንና ሰብአዊ እርዳታም እያደረገ መሆኑን በተደጋጋሚ አስታውቋል፡፡ ነገርግን ተመድን ጨምሮ አለምአቀፍ ተቋማት በትግራይ ርሃብ ማንዣበቡን እየገለጹ ይገኛሉ፤ በትግራይ ያለው የኤርትራ ጦር ለቆ እንዲወጣ ያልተቆጠበ ጫና እያደረጉ ነው፡፡