“እኔ የምሰራው ሕዳሴው ግድብ ላይ ነው ፤ ግድቡ ደግሞ የሁሉም ነው” ወ/ሮ ሮማን ገ/ሥላሴ
የሕዳሴው ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሮማን ገ/ሥላሴ በህወሃት ጥሪ ከተደረገላቸው መካከል ናቸው
ህወሃት በፌደራል ደረጃ የሚወክሉትን አመራሮችና የተወካች ም/ቤት አባላት ኃላፊነታቸውን እንዲተዉ አዟል
“እኔ የምሰራው ሕዳሴው ግድብ ላይ ነው ፤ ግድቡ ደግሞ የሁሉም ነው” ወ/ሮ ሮማን ገ/ሥላሴ
የትግራይ ክልል ገዥ ፓርቲ ህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) በፌደራል ደረጃ የሚወክሉትን አመራሮችና የሕዝብ ተወካች ምክር ቤት አባላት በተመለከተ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
ህወሃት የፌዴራል መንግስቱ ሕገ መንግስቱን እንደጣሰ ገልጾ በፌደራል ደረጃ ምርጫን በማሸነፍ በሚያዙ ኃላፊነቶችና ውክልና የነበራቸው የህወሃት አመራሮችና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ኃላፊነታቸውን በመተው ወደ ድርጅታችሁ ህወሓት ጽ/ቤት ሪፖርት እንዲያደርጉ ነው ውሳኔ ያስተላለፈው፡፡
በዚህም መሰረት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ልዩ አማካሪ አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) ፣ የሕዳሴው ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፊ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ሮማን ገ/ሥላሴ ፣ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አልማዝ መኮንን ፣ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ሙሉ ገ/እግዚአብሔር ፣ ዓባይ ወልዱን እና አዲስ ዓለም ባሌማን ጨምሮ 13 አመራሮች ለህወሃት ጽ/ቤት ሪፖርት እንዲያደርጉ ተጠይቀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የህወሃት አባል የሆኑ 27 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ጥሪ ተላልፎላቸዋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ አል ዐይን አስተያየት የጠየቃቸው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ሮማን ገ/ሥላሴ ጉዳዩን እንዳልሰሙት ተናግረዋል፡፡
ህወሃት ይህንኑ ውሳኔ በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ ሪፖርት እንዲያደርጉ ከጠቀሳቸው አመራሮች መካከል ወ/ሮ ሮማን ገ/ስላሴ አምስተኛ ተራ ቁጥር ላይ የጠቀሳቸው እርሳቸው ግን ጥሪውን እንዳላዩትና እንዳላነበቡት ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም “እኔ የምሰራው ሕዳሴው ግድብ ላይ ነው፣ግድቡ ደግሞ የሁሉም ብሔር ፣ የሁሉም ሕዝብ ሀብት ነው” ሲሉ ለአል ዐይን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ጥሪውን በተመለከተ አስተያየት እንዲሰጡን የጠየቅናቸው ወ/ሮ ሮማን ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
ትናንትና በሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ላይ የተገኙት ብቸኛዋ የትግራይ ሕዝብ ተወካይ ወ/ሮ ያየሽ ተስፋሁነኝም ህወሃት ከአባልነታቸው ተነስተው ሪፖርት እንዲያደርጉ ከጻፈላቸው የፓርቲው አባላት መካከል ቢሆኑም የህዝብ ድምፅ በማክበር ወደ ስብሰባው መምጣታቸውን ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡
“የተለያየ ፓርቲ ወክለን ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብንገባም ምክር ቤት ስንገባ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ወኪል ነን” ያሉት ወ/ሮ ያየሽ አንድ የምክር ቤት አባል ከአባልነቱ የሚነሳው የወከለው ህዝብ አይወክሉኝም ሲል አሊያም የስራ ዘመን ሲያበቃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዓለም አቀፍ በሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫ እንዲራዘም መደረጉ የሕግ ልዕልና የታየበት መሆኑን ተናግረው በመክፈቻው ስብሰባ መገኘታቸው ትክክለኛ እና የሚጠበቅ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አልማዝ መኮንንም ሪፖርት እንዲያደርጉ ከተጠቀሱት መካከል ሲሆኑ ስለጉዳዩ እንዳልሰሙ ገልጸዋል፡፡ ጥሪ የተደረገው ለምክር ቤት አባላት መሆኑን ነው የማውቀው ያሉት ወ/ሮ አልማዝ ትናንትና እስከምሽት ሥራ ላይ እንደነበሩና ስለእርሳቸውም ሆነ ስለሌሎች አመራሮች የሰሙት እንደሌለ ለአል ዐይን ተናግረዋል፡፡
አል ዐይን አማርኛ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚመለከታቸውን አካላት በማናገር ቀጣይነት ያለው ዘገባ ለአንባቢያኑ ያደርሳል፡፡