“ከፕ/ር ብርሃኑ ጋር ምንም አይነት ቂምና ቁርሾ የለኝም“ - አንዱዓለም አራጌ፤ የኢዜማ ምክትል መሪ
አቶ አንዱዓለም የኢዜማ መሪ ሆኖ ለመመረጥ ፉክክር ላይ ናቸው
የፕ/ር ብርሃኑ እና የአንዱዓለም አራጌ የሃሳብ ልዩነት ምንድነው?
በኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ መሪ እና ምክትል መሪ መካከል ምንም አይነት የግል ጸብም ሆነ ቁርሾ እንደሌለ አቶ አንዱአለም አራጌ አስታወቁ፡፡
የኢዜማ ምክትል መሪ አንዱዓለም አራጌ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት ከፓርቲው መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ጋር የሃሳብ ልዩነትና ክርክር በስተቀር ምንም አይነት ቂምና ቁርሾ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ ፕ/ር ብርሃኑ እና አቶ አንዱዓለም አራጌ የኢዜማ መሪ ሆኖ ለመመረጥ ፉክክር ላይ ናቸው፡፡ ይህንን ተከትሎም በርካቶች ከሰሞኑ ሁለቱ ወገኖች የተካረረ ጸብ ውስጥ እንዳሉ የሚገልጹ ወገኖች አሉ፡፡
አቶ አንዱዓለም የፓርቲው አባል ያልሆኑ ሰዎችም ጭምር ጉዳዩን እያጦዙት እንደሆነ ገልጸው ፕ/ር ብርሃኑ የመጀመሪያ የሥራ ኃላፊያቸው እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሲየሽን ፕ/ት ሳሉ ማህበሩ 1992 ዓ.ም ላይ ባዘጋጀው የምርጫ ክርክር ላይ አስተባባሪ እንደሆኑ የሚጠቅሱት አቶ አንዱዓለም ለአሁኑ የኢዜማ መሪ ያላቸው ክብር አሁን የመጣ እንዳልሆነ አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከኢዜማ መሪ ጋር ድሮም በነበራቸው ውይይት በሁሉም ነገር እንደማይስማሙ የገለጹት አቶ አንዱአለም እንኳን አንድ ፓርቲ ውስጥ እስር ቤት ሆነን ስንወያይም የልዩነት ሃሳቦችም ነበሩን ብለዋል፡፡ አሁን ላይም ሁለቱ ወገኖች በሃሳብ እንደሚከራከሩና እንደሚለያዩ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡
አቶ አንዱዓለም እንደሚሉት ልክ ከፕ/ር ብርሃኑ ጋር በሃሳብ እንደሚከራከሩ ሁሉ ከቀድሞው የአንድነት ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ጋርም ይከራከሩ እንደነበር አንስተዋል፡፡ የአንድነት ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት የአሁኑ ኢዜማ ምክትል መሪ አቶ አንዱዓለም አሁን በፓርቲው ውስጥ ፕ/ር ብርሃኑን የሚደግፍና የሚቃወም፤ እሳቸውንም የሚደግፍና የሚቃወም እንዳለ አንስተዋል፡፡
መሪውና ምክትል መሪው የሚያደርጉት ክርክር ፓርቲውን ይጠቅማል ወይስ አይጠቅምም፤ ሀገር ይጠቅማል ወይስ አይጠቅምም በሚል ላይ እንደሆነም አቶ አንዱዓለም ገልጸዋል፡፡
በመካከላቸው ያለው የሃሳብ ልዩነት ምንድነው?
እንደ አቶ አንዷለም ገለጻ በመካከላቸው ያለው የሃሳብ ልዩነት ፓርቲው በመጣበት መንገድ ይጓዝ ወይስ አይጓዝ? እስካሁን የመጣበት መንገድ ወደሚፈልገው አቅጣጫ አድርሶታል ወይስ አላደረሰውም የሚል ነው፡፡
ፕ/ር ብርሃኑን በመተካት ፓርቲውን ለመምራት የሚወዳደሩት አቶ አንዱዓለም አራጌ ፓርቲው ለውጥ ያስፈልገዋል የሚል ሃሳብ አላቸው፡፡ ይህን ምክትል መሪያቸው ለመሆን አብረዋቸው የሚወዳደሩት አቶ ሀብታሙ ኪታባም ይጋራሉ፡፡
በሌላኛው ወገን በመሪነታቸው ለመቀጠል የሚወዳደሩት ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ፓርቲው በመጣበት መንገድ ግቡን ያሳካል የሚል እምነት አላቸው፡፡
ምክትል መሪው አቶ አንዱዓለም በሀገራችን ስለደሞክራሲ መወለድና መምጣት ብዙ ቃል ቢገባም ይህ አለመሳካቱን ገልጸዋል፡፡ ዴሞክራሲ እንዲመጣና ፓርቲውም በዚህ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ፤ በምርጫም አሸናፊ እንዲንሆን የሚል ቃል የተገባ ቢሆንም በተገባው ቃል ምክንያት የፓርቲው ቅቡልነት እየተሸረሸረ መምጣቱንና ይህ ነገርም ፓርቲውን አጠናክሮ ለማውጣት አስቸግሮ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ኢዜማን ወደታሰበው ለመመለስ ፤ አይነ ግቡና በህዝብ የሚደገፍ ብሎም የሚታመን ለማድረግ ጥረት እናደርጋለን ብለዋል፡፡
ሌላው አቶ አንዱዓለምን እና ፕ/ር ብርሃኑን የሃሳብ አለመግባባት ውስጥ የከተተው ጉዳይ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጉዳይ መሆኑን አቶ አንዱዓለም ግልጿል፡፡ ቀደም ሲል “ጁንታው ሞቷል፤ ተቀብሯል፤ እንደ አላዛር አይነሳም፤ ታሪክ ሆኗል” ከተባለ በኋላ ያ ሃይል ከመቃብር ወጥቶ ሌላውን ማሳደድ ሲጀምር ጦርነት በጦርነት እንደማያልቅ ግልጽ እንደነበር አቶ አንዱዓለም አንስተዋል፡፡
ሚሊኖች አልቀው ቢሊየኖች ከወደሙ በኋላ ወደ ድርድር ከመሄድ አስቀድሞ ኢዜማ ለሰላም ጥረት ማድረግ እንዳለበት ሲወተውቱ እንደነበርም ያነሱት፡፡
ብዙ ነገር ከወደመ በኋላ ለድርድር መምጣተቸው ስለማይቀር ኢዜማ አስቀድሞ ይህንን ሃሳብ ቢይዝ ኖሮ በህዝቡም ዘንድ ትልቅ 'ክሬዲት' ሆኖ ይቆጠርለት እንደነበርና ሀገርም ከዚህ ይጠቀም እንደነበር ገልጸዋል፡፡
አቶ አንዱዓለም “በሰላማዊ ትግል የሃይማኖቴን ያህል አምናለሁ”ያሉ ሲሆን ሰላማዊ የውይይት መፍትሄ ሀገሪቱን ከችግር የሚያወጣ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
አል ዐይን ፕሮፌሰር ብርሃኑን አግኝቶ ስለ ጉዳዩ ለመጠየቅና ሃሳባቸውን ለማካተት በተደጋጋሚ ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ በተገኙበት በማንኛውም ጊዜ ሃሳባቸውን የሚያስተናግድም ይሆናል፡፡