የተመድ የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ቡድን ወደ ዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ጣቢያ አቀና
የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ኃላፊ ግሮሲ "የዩክሬን እና የአውሮፓ ትልቁን የኒውክሌር ጣቢያ ደህንነት መጠበቅ አለብን" ብለዋል
የቡድን-7 አባል ሀገራት ፤የተመድ ሰራተኞች "ያለ ምንም እንቅፋት"ጣቢያው ላይ መድረስ መቻል አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ቡድን በዩክሬን ወደ ሚገኘውና በሩሲያ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ወዳለው ዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ጣቢያ ማቅናቱ ተገለጸ፡፡
ዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ጣቢያ በጦርነቱ ምክንያት በአከባቢው ላይ መጠነ ሰፊ የተኩስ ልውጦች እየተካሄዱ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ፤ በኒውክሌር ጣቢያው ላይ ጥቃት ከደረሰ የጨረር አደጋ እንዳያስከትል በርካቶች ስጋታቸው ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡
ዩክሬን፤ የሩሲያ ኃይሎች በኒውክሌር ጣብያው ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል ስትል ክስ ማቅረቧ የሚታወስ ነው፡፡
ከዛም አለፍ ብሎ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ በቅረቡ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት “አሁን ዓለም አንድን የኒውክሌር ሃይል ጣቢያ ለመከላከል ጥንካሬ እና ቆራጥነት ካላሳየ ተሸንፏል ማለት ነው፤ ለኒውክሌር ጥቃት እጁን ይሰጣል” በማለት በኒውክሌር ጣቢያው ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ያለው ትርጉም ግዙፍ መሆኑ ሲናገሩ ተሰምቷል።
ሩሲያ በበኩሏ ፤ የዩክሬን ጦር ግዙፉን የኒውክሌር ጣቢያ ለማውደም ተኩስ ከፍተዋል በማለት ኪቭን ስትከስ ተደምጣለች።
ሞስኮ፤ ዩክሬን ግዙፉን አቶሚክ ሃይል ማመንጫ ጣቢያ ማውደሟ “አሰቃቂ መዘዝ” ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ልታውቅ ይገባል ስትል አማስጠንቀቋም ጭምር አይዘነጋም።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "የዩክሬን ታጣቂ ሃይሎች የኒውክሌር ጣቢያን ማውደም ከዩክሬን ባለፈ ለአውሮፓ ምድር እጅግ አደገኛ ሊሆን የሚችል ተግባር ነው”ሲሉም ነበር የተደመጡት ከሁለት ሳምንታት በፊት በሰጡት መግለጫ፡፡
እናም በጦርነት ውስጥ የሚገኙትና እርስ በርስ የሚካሰሲት ሩሲያና ዩክሬን በጣቢያው ላይ የሚያደርሱት ጥቃት ከሀገራቱ በዘለለ ለተቀረው ዓለም ያልተፈለገ መዘዝ ይዞ እንዳይመጣ ተስግቷል።
በዚህም ሁኔታው ያሰጋው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ቀደም ሲል ባወጣው መግለጫ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያው አከባቢ ከጦር ነጻ እንዲሆን ጥሪ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
ሁለቱም አካላት የኃይል ጣቢያው አካባቢ ውጊያ እንዲያቆሙ መጠየቁም እንዲሁ አይዘነጋም፡፡
አሜሪካም ብትሆን ቦታው ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ እንዲሆንና ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) ቦታውን እንዲጎበኝ አሳስባ ነበር።
በዚህም መሰረት ዓለም ከዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ የተውጣጣ የተመድ ቡድን በዛሬው ዕለት ወደ ዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ጣቢያ ማቅናቱ ኤኤፍፒ ዘግቧል ፡፡
የተመድ የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ቡዱን ወደ ዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ማቅናቱን የገለጹት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ፤ "የዩክሬን እና የአውሮፓ ትልቁን የኒውክሌር ጣቢያ ደህንነት መጠበቅ አለብን" ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ አጋርተዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ፤ በኒውክሌር ጣቢያው መች እንደሚደርሱ ግን በግልጽ ያሉት ነገር የለም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ሰራተኞች ወደ ኒውክሌር ጣቢያው በሚያደርጉት ጉዞ ምንም አይነት እንቅፋት እንዳይገጥማቸው የቡድን-7 አባል ሀገራት ዳይሬክተሮች ቡዱን ባወጣው መግለጫ አሳስቧል፡፡
ሰራተኞቹ "ያለ ምንም እንቅፋት" መድረስ መቻል አለባቸውም ሲልም ነው የሩሲያም ሆነ የዩክሬን ኃይሎች ያሳሰበው መግለጫው፡፡
በደቡብ ምስራቅ ዩክሬን የሚገኘው ዛፖሪዝሂያ አቶሚክ ሃይል ማመንጫ በአውሮፓ ትልቁና በዓለም ላይ ካሉት 10 ትላልቅ የኒውክሌር ኃይል ጣቢያዎች መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡