ዘለንስኪ፤ ዓለም የዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ጣቢያን መከላከል ካልቻለ “በሽብርተኞች ይሸነፋል” ሲሉ አስጠነቀቁ
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ዓለም አፋጣኝ እርምጃ ካልወሰደ "ለኒውክሌር ጥቃት እጁን ይሰጣል" ብለዋል
ሩሲያ፤ በዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ጣቢያ ከደረሰው ጥቃት ጋር በተያያዘ እጄ የለበትም እያለች ነው
ዓለም በሩስያ ቁጥጥር ስር በሚገኘው ዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመከላከል ምንም ዓይነት እርምጃ ካልወሰደ፤ “በሽብርተኞች ይሸነፋል” ሲሉ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ አስጠነቀቁ።
በደቡብ ምስራቅ ዩክሬን የሚገኘው ዛፖሪዝሂያ አቶሚክ ሃይል ማመንጫ በአውሮፓ ትልቁና በዓለም ላይ ካሉት 10 ትላልቅ የኒውክሌር ኃይል ጣቢያዎች መካከል አንዱ ነው።
እናም በጦርነት ውስጥ የሚገኙትና እርስ በርስ የሚካሰሲት ሩሲያና ዩክሬን በጣቢያው ላይ የሚያደርሱት ጥቃት ከሀገራቱ በዘለለ ለተቀረው ዓለም ያልተፈለገ መዘዝ ይዞ እንዳይመጣ ተስግቷል።
ሁኔታው ያሰጋው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያው አከባቢ ከጦር ነጻ እንዲሆን ጥሪ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
ተመድ፣ ሁለቱም አካላት የኃይል ጣቢያው አካባቢ ውጊያ እንዲያቆሙ ጠይቋል።
በስብሰባው ያላትን ስጋት የገለጸችው አሜሪካም፤ ቦታው ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ እንዲሆንና ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) ቦታውን እንዲጎበኝ አሳስባለች።
ዓለም በጉዳዩ ላይ በርካታ ማሳሰቢያዎች ቢደረድርም ግን፤ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ነገሮች እየረፈዱ መሆናቸው የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በማስጠንቅቅ ላይ ናቸው።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ ትናንት ማምሻውን ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት “አሁን ዓለም አንድን የኒውክሌር ሃይል ጣቢያ ለመከላከል ጥንካሬ እና ቆራጥነት ካላሳየ ተሸንፏል ማለት ነው” ብለዋል።
ዓለም አፋጣኝ እርምጃ ካልወሰደ "በሽብርተኞች ይሸነፋል እንዲሁም እና ለኒውክሌር ጥቃት እጁን ይሰጣል" ሲሉም ተደምጠዋል።
ዩክሬን እና አጋሮቿ በኒውክሌር ጣቢያው ጉዳይ ሩሲያ ላይ ቢያነጣጥሩም፤ የክሬምሊን ሰዎች ግን ጉዳዩ ሞስኮን የመወንጀል ያክል ቀላል እንዳልሆነና ሌላ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው።
የሩሲያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ፤ “የኒውክሌር አደጋዎች በአውሮፓም ሊከሰቱ ይችላሉ” ሲሉ ያስጠነቀቁት ከቀናት በፊት እንደነበር አይዘነጋም።
ሜድቬዴቭ ይህን ያሉት በዩክሬን ዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ዙሪያ ኃይሎችን በማስፈር የኒውክሌር አደጋን በመፍጠር ሩሲያን ለሚወነጅሉት የዩክሬን አጋሮች ባስተላለፉት መልዕክት ነው።