ሩሲያ የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አቃቤ ህግን በተፈለጊ ዝርዝር ማካተቷ አባላቱን “በጣም አሳስቧቸዋል”
ሩሲያ ባሳለፍነወ ቅዳሜ የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ ላይ የእስር ማዘዣ አውጥታለች
ሩሲያ በፑቲን ላይ እስር ማዘዣ እንዲወጣ ያደረጉት አቃቤ ህግ ካሪም ከሃን በጥብቅ እፈልጋለሁ ብላለች
የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አባላት ሩሲያ የፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግን በተፈለጊ ዝርዝር ማካተቷ በጣም እንዳሳሰባቸው ተገለጸ።
ሩሲያ ባሳለፍነው ቅዳሜ በፕሬዝዳንት ፑቲን ላይ እስር ማዘዣ እንዲወጣ ያደረጉት የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ ካሪም ከሃን በጥብቅ እፈልጋለሁ ማለቷ ይታወሳል።
በዚህም መሰረት መቀመጫውን ዘ ሄግ ያደረገው የአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ ካሪም ከሃን በሩሲያ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር የተፈላጊ ዝርዝር ውስጥ መካተታቸው ተነግሯል።
ይህንን ተከትሎም የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አባል ሀገራት በትናትናው እለት ባወጡት መግለጫ ሩሲያ የፍርድ ቤቱን አቃቤ ህግ እና በርካታ ዳኞችን በሀገሪቱ የተፈላጊ ዝርዝር ውጥ ማካተቷ በእጅጉ እንዳሳሰባቸው አስታውቀዋል።
የፍርድ ቤቱ አባል ሀገራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት በመግለጫቸው፤ የአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ኮሚሽኑንን የመመርመር አቅምን ለማዳከም የሚደረጉ የማስፈራራት ድርጊቶች ተቀባይነት የሌላቸው መሆናቸውን አስታውቋል።
የፍርድ ቤቱ ባለስልጣናት እና ዳኞች ላይ እየተወሰዱ ያሉ ያልተገባ እና ፍትሃዊ ያልሆኑ የማስገደድ እርምጃዎች በእጅጉ እንደሚያሳስበውም ገልጿል።
የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዳኞች ባሳለፍነው መጋቢት ወር በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ የእስር ማዘዣ ማውጣታቸው ይታወሳል።
ፍርድ ቤቱ የእስር ማዘዣ ያወጣው በዩክሬን ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሩሲያ ፕሬዝዳንት ዋነኛው ተጠያቂ ናቸው በሚል ነው።
የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በወቅቱ በሰጠው መግለጫ የዓለም አቀፍ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ትዕዛዝን ውድቅ አድርጓል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛራኮቫ እንዳሉት "የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ረብ የለሽ እና የማይተገበር ነው፣ ሩሲያ ባልፈረመችው ህግ ማንም ሊጠይቃት አይችልም" ሲሉ ለራሺያ ቱዴይ ተናግረዋል።