የአማራ ህዝብ "የወያኔን ዳግም ወረራ ለመመከት" ዝግጁ እንዲሆን የክልሉ መንግስት ጥሪ አቀረበ
በክልሉ ላልቷል የተባለውን ህግና ስርዓት እንደሚያስከብርም ምክር ቤቱ ገልጿል
"የወያኔ ወራሪ ቡድን" በአማራ ክልል ላይ ዳግም ጦርነት አውጇል ብሏል የክልሉ የጸጥታ ምክር ቤት
የአማራ ህዝብ የወያኔን ዳግም ወረራ ለመመከት ዝግጁ እንዲሆን የክልሉ መንግስት ጥሪ አቀረበ።
ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 05/2014 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የክልሉን ወቅታዊ የጸጥታና ደህንነት ሁኔታ በጥልቀት መገምገሙን ያስታወቀው የክልሉ መንግሥት የፀጥታ ምክር ቤት "የወያኔ ወራሪ ቡድን በየቀኑ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ የትግራይን ሕዝብ ለጦርነት እያነሳሳ በአማራ ክልል ላይ ዳግም ጦርነት አውጇል" ሲል መግለጫ አውጥቷል፡፡
ምክር ቤቱ በመግለጫው "ይህን አደገኛ ቅዠቱን ለመመከትና ለመቀልበስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ" በአንክሮ መወያየቱን የገለፀ ሲሆን በየደረጃው ያለው የፀጥታ መዋቅር ዝግጁ መኾን እንዳለበት አቅጣጫ ማስቀመጡን አስታውቋል፡፡
"ሕዝባችን ዳግም ለወያኔ ወረራ ለጥቃት እንዳይዳረግ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደወትሮው ኹሉ የፀጥታ መዋቅሩ፣ ደጀኑ ሕዝብ የራሱን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መኾን አለበት" ሲልም ነው ምክር ቤቱ በመግለጫው ያስታወቀው።
የወያኔን ዳግም ወረራ ለመቀልበስና ለመከላከል የውስጥ አንድነትን ማጠናከር፣ ሰላምና ደኅንነትን መጠበቅ ቁልፍ ጉዳይ ነው ብሎ እንደሚያምንም አስቀምጧል።
"በአንድ በኩል ከፌደራል የጸጥታ መዋቅር ጋር በመቀናጀት ከወያኔ የሚሰነዘርብንን ጥቃት ለመከላከል በተጠንቀቅና በዝግጁነት መቆም፤ በሌላ በኩል ደግሞ በውስጣችን ለወያኔ ሴራ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩትን ሕገ-ወጦችንና ሥርዐት አልበኞችን በመቆጣጠር የክልላችን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ" ግንባር ቀደም የትኩረት አቅጣጫ እንዲኾኑ ተወስኗልም ነው ያለው፡፡
በየደረጃው የጸጥታ ግብረ ኀይል አቋቁሞ ሕገወጥነትን ለመቆጣጠርና ሕግን ለማስከበር ተገቢ ነው ያላቸውን ሕጋዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ አቅጣጫ ማስቀመጡንም ገልጿል፡፡
በመኾኑም የክልሉ ሕዝብ፣ ወጣቶች፣ የገጠርና የከተማ ነዋሪዎች ሰላምና ደኅንነትን ለመጠበቅ እና የውስጥ አንድነትን ለማጠናከር የፀጥታ መዋቅሩ በሚወስደው እርምጃ ኹሉ ተባባሪ እንዲኾኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በሌላ በኩል በየደረጃው በተደረጉ ሕዝባዊ ውይይቶች የሕግ ማስከበር ሥራ መላላት ጎልተው ከወጡ ወሳኝ ጉዳዮች መካከል አንዱ መሆኑን ያነሳው ምክር ቤቱ ጉዳዩን መልክ ለማስያዝ በየደረጃው ሕግ የማስከበር ሥራውን በጥብቅ እንደሚፈጽም አስታውቋል።
ከሰሞኑ ተከታታይ ህዝባዊ የውይይት መድረኮችን እያካሄደ እንደሚገኝ ያስታወቀው ህወሓት ለትግራይ ህዝብ ጥሪ አድርጓል መባሉ የሚታወስ ነው።