“ሀገራችንን በእውነት የምንወድ ከሆነ ምንም ዓይነት ምላሽ ሊለውጠን አይገባም”- ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ
የጥምቀት ከተራ በዓልን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት “የማይደረገውን በማድረግ ኢትዮጵያን እናክብር” ብለዋል
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የምትፈልገው “በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ፍቅር አይደለም”ም ብለዋል
“ምንም ዐይነት ምላሽ” ለሃገራችን ያለንን መውደድ ሊለውጠው አይገባም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የጥምቀት ከተራ በዓልን አስመልክተው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት “ሀገራችንን በእውነት የምንወድ ከሆነ ምንም ዓይነት ምላሽ ሊለውጠን አይገባም” ብለዋል፡፡
በመልዕክታቸው ኢትዮጵያ የምትፈልገው ፍቅር “በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ አይደለም” ያሉም ሲሆን ከዚያ ይልቅ “ጊዜና ሁኔታ የማይቀይሩት ዓይነት ፍቅር” እንደምትፈልግ ገልጸዋል።
ይህንኑ በማስታወስም “ሀገራችንን በእውነት የምንወድ ከሆነ ምንም ዓይነት ምላሽ ሊለውጠን” እና “ለሀገራችን ያለን ፍቅር ሊለወጥ” አይገባውም ሲሉ አስቀምጠዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው።
ትኅትና የኃያልነት ምልክት እንደሆነ ከክርስቶስ መማር እንደሚገባ ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ጥላቻን በፍቅር መለወጥ፣ በቀልን በይቅርታ ማክሸፍ፣ ግጭትን በዕርቅ መዝጋት ተገቢ ነው” ብለዋል፤ ኢትዮጵያን “ኢትዮጵያ” አድርጎ ያቆያት ዕሴት ይሄው መሆኑን በመጠቆም።
“የማይደረገውን በማድረግ ኢትዮጵያ ማክበር ይገባል”ያሉም ሲሆን ትኅትና ‹እኔ› ከሚለው ሥነ ልቡናዊ በሽታ፣ ከድል ሽሚያና ከባለውለታነት ትዕቢት እንደሚያወጣ ገልጸዋል።
“ሥራችንን ሀገር በማዳናችን እንጂ በጠላታችን ትዕቢት አንለካው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ ስንል “ይቅርታን እንዘምር፤ ስሜታችንን እናርቅ፤ በደልን ይቅር እንበል፤ ጉዳታችንን እንሸከም፤ አመላችንን እንግራ፤ ሀገር ለማክበር ስንል ክብራችንን እንሠዋ። ፍቅራችንን፣ ትኅትናችንንና ክብራችንን ለሀገራችንና ለወገናችን እናሳይ” ሲሉ አስቀምጠዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡፡
ከሃይማኖታዊ ፋይዳው ባለፈ በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበውን የጥምቀትን ክብረ በዓል የቱሪስት መስህብነት የሚያሳድጉ ስራዎች እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡