“በቁም እስር ላይ ናቸው” የተባሉት የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ወደማይታወቅ ቦታ መወሰዳቸው እየተነገረ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ እንደሚሰጡም ይጠበቃል ተብሎም ነበር
የሃገሪቱ ወታደሮች ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዶክን ጨምሮ ሌሎች ሲቪል ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር አውለዋል
“በቁም እስር ላይ ናቸው” የተባሉት የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ወደማይታወቅ ቦታ መወሰዳቸው እየተነገረ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁኔታውን በማስመልከት መግለጫን እንደሚሰጡ ተነግሮ ነበር፡፡ ሆኖም ለቃለ መጠይቁ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል ያሉ አንዳንድ የመረጃ ምንጮች ወደማይታወቅ ቦታ ተወስደዋል ብለዋል፡፡
ብዙዎች “መፈንቅለ መንግስት ነው” ባሉት እርምጃ የሱዳን ጦር ዛሬ ማለዳ የሀገሪቱን የሽግግር መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክን ጨምሮ ሲቪል ባለስልጣናትንና ከፍተኛ አመራሮችን በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡
ሃምዶክ የቁም እስረኛ ሆነው በቤት ውስጥ እንዲቆዩ መደረጋቸው ነበር የተነገረው፡፡ ይህንንም በካርቱም የሚገኘው የአል ዐይን ኒውስ ዘጋቢ አረጋግጧል፡፡
“የግልበጣ ሙከራው በጦር ኃይሉ የውስጥ እና የውጭ አካላት የተቀናበረ ነው”- ጠ/ሚ አብደላ ሃምዶክ
ሌሊት ከተጀመረው መፈንቅለ መንግስት በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክን የካቢኔ ጉዳዮች ፤ የኢንዱስትሪ እና የኢንፎርሜሽን ሚኒስትሮች መታሰራቸው ተረጋግጧል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚዲያ አማካሪ ፋይሳል መሐመድ ሳሌህ ቤተሰቦች ቤትም በጸጥታ ኃይሎች ከበባ የተደረገበት ሲሆን የአረብ ሶሻሊስት ባአስ ፓርቲ ዋና ጸሐፊ አሊ ለ ሪህ አል ሳን ሃውሪም ታስረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በሰዓታት ውስጥ መግለጫ ይሰጣሉ የተባለ ሲሆን የሀገሪቱ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር አብደል ፈታህ አልቡርሃን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያውጁ ይችላሉ ተብሏል፡፡
ከሰሞኑ ለተቃውሞ በአደባባይ የሰነበቱት ሱዳናውያን አሁንም ወደ ካርቱም አደባባይ በመውጣት ተቃውሞ ማሰማት ጀምረዋል።
አሁን ላይ የካርቱም ዓለም አቀፍ አውሮፕላና ማረፊያ የተዘጋ ሲሆን፤ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎትም ተቋርጧል ነው የተባለው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ በሀገሪቱ ወታደራዊ አመራር የቁም እስረኛ እንዲሆኑ መደረጋቸውን የተገለጸ ሲሆን ሰሞኑን በሱዳን ወታደራዊ አመራሩን የሚቃወሙ ም የሚደግፉም ሰልፎች መካሄዳቸው ይታወሳል፡፡
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ትናንትና እና ከትናንት በስቲያ ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ እና ከሉኣላዊ የሽግግር ምክር ቤቱ ሊቀመንበር አብደል ፋታህ አልቡርሃን ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
ሱዳን በቅርቡ ወታደራዊ አመራሩ አከሸፍኩት ያለው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አጋጥሟት እንደነበር ይታወሳል፡፡