ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል በጸደቀው አዋጅ ላይ ባለድርሻ አካላት ተወያይተዋል፡፡
ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል በጸደቀው አዋጅ ላይ ባለድርሻ አካላት ተወያይተዋል፡፡
ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች ዝውውር በሰፊው ከሚከናወንባቸው ሃገሮች ተርታ መሰለፏን የፌዴራል መንግስት ሲገልጽ ቆይቷል፡፡
የጦር መሳሪያዎች በቀላሉ መገኘት፣ የህብረተሰቡ ጦር መሳሪያ የመታጠቅ ፍላጎት መጨመር እና ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሃገራት ጋር ባሏት ድንበሮች ላይ ያለው ቁጥጥር ማነስ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በስፋት እንዲስፋፋ አድረገዋልም ነው የተባለው፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ለፖለቲካ ዓለማም እየዋለ መሆኑን አስታውቋል፡፡ለአብነትም የሃገሪቱን መረጋጋት የማይፈልጉ ያላቸው ሃይሎች በዚህ ዝውውር ውስጥ እንዳሉበት አስታውቋል፡፡
በሃሪቱ ከህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ጋር በተያያዘም በርካታ ወነጀሎች እየተሰሩ ስለመሆናቸውም ነው መንግስት የሚገልጸው፡፡
ኢትዮጵያ በሱዳን፣ በሶማሊያ፣ በጅቡቲ፣በኬንያ በኩል በምትዋሰንባቸው ድንበሮች የጦር መሳሪያዎች በገፍ እየገቡ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ይህም በሃገር ውስጥ አለመረጋጋት እንዲኖር እያደረገ ነው ተብሏል፡፡
በዚሁ መሰረት በግማሽ ዓመት ውስጥ በርካታ የጦር መሳሪያዎች እና የጦር መሳሪያዎች ጥይቶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፌዴራል ፖሊስ የህግ አገልግሎት ዳይሬክትር ኮማንደር ፋሲለ አሻግሬ አስታውቀዋል፡፡
በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የሕግ ጥናቶች ማርቀቅና ማስረጽ ዳይሬክተር አቶ በላይሁን ይርጋ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት እየጨመረ ያለው ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ ኢትዮጵያን ወደ አለመረጋጋት እና የደህንነት ስጋት ውስጥ ስለሚከታት የጦር መሳሪያዎች ይዞታን ለመቆጣጠር እና ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል አዲስ አዋጅ ማዘጋጀት ማስፈለጉን አንስተዋል፡፡
አዋጁም በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁን አንስተዋል፡፡
በሃገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ወቅቶች በሚከሰቱ ግጭቶች የተነሳ ይህ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በከፍተኛ ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ ቢመጣም፣ እስካሁን የሕግና የአሰራር ስርአት የሌለው በመሆኑና በሌሎችም ምክንያቶች የአዋጁ ተግባራዊነት በመዘግየቱ ባለድርሻ አካለት እንዲመክሩበት ነው የሰላም ሚኒስቴር ውይይቱን ያዘጋጀው፡፡
አዋጁ ተገቢው ምዝገባ ተደርጎ በህጋዊ መልኩ የጦር መሳሪያን ለማስተዳደር እንደሚያግዝ ተገልጿል።
ከዚህ ባለፈም አዋጁ ለባለድምፅ መሳሪያዎች ብቻ ሳይሆን ለድምፅ አልባ የጦር መሳሪያዎችም ምላሽ ይሰጣል ተብሏል።
የጦር መሳሪያዎች ይዞታ መቆጣጠር እና ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል የወጣውን አዲስ አዋጅ የሚያስፈጽሙት፡-
የፌዴራል ወይም የክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች
ሚሊሻ
የፌዴራል ወይም የክልል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር
የፌዴራል ወይም የክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ወይም ፍትህ ቢሮዎች
የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ናቸው፡፡
አሁን ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከጸደቀው አዋጅ ባለፈ በድንበሮች አካባቢ ያለውን ፍተሸ ማጠናከርም እንደሚያስፈልግ ነው የተገለጸው፡፡