የማዕረግ ምልክቶቹ አንበሳን እና ጋሻን እንዳያካትቱ ተደርጓል ተብሏል
የመከላከያ ሠራዊት ሲጠቀምበት በቆየው የማዕረግ ምልክት ላይ ማሻሻያዎችን አደረገ።
የሠራዊቱ ማዕረግ አገራዊም ይሁን ወታደራዊ ታሪካዊ ይዘት ያለውና የሠራዊቱንም ባህሪ ሊገልፅ የሚችል ሆኖ እንዲዘጋጅ በማስፈለጉ ማሻሻያው መደረጉ ተገልጿል።
በማሻሻያው መሠረትም በማዕረግ ምልክቶቹ ውስጥ ጋሻ እና አንበሳ በዋናነት ጥቅም ላይ ውለዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ በተለይም በንጉሱም ይሁን በደርግ እንዲሁም በኢህአዴግ ዘመን ጋሻ፣ ዘውድ እና አምበሳን መሠል ምልክቶች የሠራዊቱ የማዕረግ አካል ሆነው ጥቅም ላይ መዋላቸውን
ያስታወሰው መከላከያ ሰራዊቱ ሠራዊት ዘመን ተሻጋሪ መሆን ካለበት ዓርማውም፣ ማዕረጉም፣ ሌሎችም ነገሮች ስርዓት ሲለዋወጥ መቀየር የለባቸውም ብሏል።
የደርግ ሠራዊት የማዕረግ ምልክቶች መሰረታዊ ይዘታቸው አገራዊ እንደነበር በመግለጽም ይህ የተሻሻለው የማዕረግ ምልክት እነዚህን አገራዊ፣ ታሪካዊና ወታደራዊ ይዘቶች በአንድ በኩል ታሪክን ከማስቀጠል አንፃር እንዲመለሱ ከማድረጉም በላይ ባላቸው አገራዊና ወታደራዊ ታሪካዊ ይዘት ምክንያት ከመጣውጋር የመቀየር እጣ እንደማይኖራቸው አስቀምጧል።
በመሆኑም የሠራዊቱ የማዕረግ ምልክት በዋናነት ሰራዊቱን እና ህዝቡን ይገልጻል ያለውን አንበሳን እና የአገር ሉዓላዊነትና ክብር የማስጠበቃችን ምልክት ነው ያለውን ጋሻን እንዲያካትት ተደርጎ መዘጋጀቱን ለመንግስት ሚዲያዎች በላከው መግለጫ አስታውቋል።