“የተገኘው ድል ዘላቂ እንዲሆን በፖለቲካዊና ሰላማዊ መንገዶች እንዲቋጭ ይደረጋል”- ጠ/ሚ ዐቢይ
ጠላቶች “አፈር ልሰው እንዳይነሡ እንመክታለን”ም ነው ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ያሉት
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድሉ እንዳይቀለበስ በሁለንተናዊ መስክ “እናጠብቀዋለን” ብለዋል
የተገኘው ድል ዘላቂ እንዲሆን በፖለቲካዊና ሰላማዊ መንገዶች እንዲቋጭ እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ፡፡
መንግስት ያገኘው ድል እንዳይቀለበስ በማድረግ በሁለንተናዊ መስክ “እናጠብቀዋለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድሉን ለመጠበቅና ዘላቂ እንዲሆን በ “አሸናፊ ምሕረት” ግጭቱ የፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ እንደሚሰራ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
መንግስታቸው ያጠፋ እንዲቀጣ፤ የበደለ እንዲካስ የሚያደርግ ሁሉን አቀፍ ፍትሕ በሽግርር እና በተሃድሶ ፍትህ እይታ፤ ሃገራዊ ባህሎችን እና እሴቶችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ፤ እንደሚሰራም ነው ያስታወቁት፡፡
መንግስት በሽብር ከፈረጃቸው ሕወሓትና ኦነግ ሸኔ ጋር ጦርነት ያካሄደወ “ቀይ መሥመር” በመጣሱ ምክንያት መሆኑን ጠ/ሚ/ር ዐቢይ ገልጸዋል፡፡
ሕወሓት ከ“ባዕዳን” ጋር በመሆን ሰሜን ዕዝን በማጥቃት የሀገርን ግዛታዊ አንድነት፣ ክብርና ሉዓላዊነት ለአደጋ እንዲጋለጥ በር መክፈቱን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የቅርብና የሩቅ ጠላቶች “እንደ ፈለጉት እጃችንን ሊጠመዝዙ የሚችሉበትን ምክንያት” ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመንግስት በኩል ቀደም ሲል ጀምሮ በዋና ዋና ልዩነቶች ላይ ሀገራዊ ምክክር እንዲደረግ ፤ ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ እንጂ ወደ ጠብና ጦርነት እንዳያመሩ የሚል አቋም እንደነበር ያነሱ ሲሆን ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ “ፍቅር ይልቅ ጠብና ጥላቻን በመረጡ፤ ከሰላም ይልቅ የጦርነትን መንገድ በተከተሉ፤ ከይቅርታ ይልቅ ነባር ቁርሾዎችን ለፖለቲካ ትግል መጠቀም በሚፈልጉ ኃይሎች ቀውስ ተፈጥሮብናል” ብለዋል፡፡
መንግስት ችግሮች ለመፍታት ሰላማዊውን መንገድ መርጦ እንደነበር የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ሌሎች ግን ሰላማዊውን መንገድ አለመምረጣቸውን ተናግረዋል፡፡
“የዘረጋናቸውን የሰላም እጆች ነክሰዋል፤ ከእኛ ይቅር በሚል መርህ ግማሽ መንገድ ስንቀርባቸው እጥፉን እየሸሹ፣ ልዩነቶች በሰላማዊ መፍትሔ ሊታረቁ ሲችሉ የጸብ መንደር ውስጥ ይዘውን ገብተዋል” ሲሉም ነው የገለጹት።
መንግስት ጦርነት ላይ ከአንድ ዓመት በላይ የቆየው የዘረጋው የሰላም እጅ ተቀባይነት በማጣቱ መሆኑን ገልጸው የመጀመሪያ ምርጫው ምንጊዜም ችግሮችን በሠለጠነ መንገድ ለመፍታት ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ማንኛውም የሰላም፣ የይቅርታና የፍቅር መንገድ ሊጥሳቸው የማይገቡ ቀይ መሥመሮች እንዳሉ ጠቅሰው ፤ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚከፋፈል፣ የሀገርን ክብርና ሉዓላዊነት የሚጥስና የግዛት አንድነትን ለአደጋ የሚያጋልጥ ማንኛውም መፍትሔ ተቀባይነት እንደሌለው ጠቅሰዋል፡፡
የ”ክህደትና የክፍፍል መንገድን የሚከጅል” ሁሉ፣ የኢትዮጵያውያን ክንድ “መቅመሱ አይቀርም” ፤ ከዚያ በታች ባሉ ጉዳዮች ዙሪያ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ድሮም” ልባችን ክፍት ነበር፤ ወደፊትም የሰላም እጃችን አይታጠፍም” በማለት ገልጸዋል፡፡
በአንድ በኩል ድል አድራጊውን የኢትዮጵያ ክንድ “እያሳየን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ትሁቱን የኢትዮጵያውያን ልብ እናሳያለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጠላቶች “አፈር ልሰው እንዳይነሡ እንመክታለን” ብለዋል፡፡
መንግስት ጦርነት ውስጥ የገባው ሰላምን በሌላ በምንም መልኩ ለማምጣት ስላልቻልን እንዲሁም ጦርነት ሰላምን የማረጋገጫ የመጨረሻው አማራጭ ስለነበረ መሆኑን የሀገሪቱ ርዕሰ መስተዳድር ዐቢይ አሕመድ ገልጸዋል፡፡
“ደም የተቃቡ ጠበኞችን ጭምር እስከማጋባት የሚደርስ የዕርቅና የሰላም ዕሴት ያለን ሕዝቦች ነን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያዊ ድል አድራጊነት ምህረትን እንደሚውቅና ኢትዮጵያውያን በአድዋ ጦርነት የተማረኩትን የጣልያን ወታደሮች በአሸናፊ ምሕረት ማድረጋቸውን ታሪክ ጠቅሰው ገልጸዋል፡፡