በኢትዮጵያ፤ ባለፈው ሳምንት ብቻ 308 ሰዎች በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ሞተዋል
ይህም በየቀኑ በአማካይ 44 ሰዎች በወረርሽኙ ሳቢያ ህይወታቸውን እያጡ መሆኑን እንደሚያመላክት ዶ/ር ሊያ ታደሰ ተናግረዋል
ይህ በአንድ ሳምንት ውስጥ ያጋጠመ ከፍተኛው የወረርሽኙ ሟቾች ቁጥር ሆኖ መመዝገቡ ነው የተነገረው
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ በአንድ ሳምንት ውስጥ ከፍተኛው የሟቾች ቁጥር መመዝገቡን የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ገለጹ።
ሚኒስትሯ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋና በወረርሽኙ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም እያሻቀበ ነው ሲሉ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በኢትዮጵያ በአንድ ሳምንት ውስጥ ከ9 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል ተባለ
በመግለጫቸው ህብረተሰቡ ቫይረሱን ለመከላከል የሚያደርገው ጥንቃቄ መላላት በተለይም ደግሞ ዴልታ የተሰኘው የቫይረሱ ዝርያ በኢትዮጵያ መገኘት ለወረርሽኙ መስፋፋት ምክንያት ሆኗል ብለዋል።
አለመከተብ እና ከቫይረሱ ጋር የሚሰራጩ ሃሰተኛ መረጃዎች ለስርጭቱ መስፋፋት ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውንም ተናግረዋል።
በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ለ6 ሺህ እየተቃረበ ነው እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፡፡
ባለፈው ሳምንት ብቻ 308 ሰዎች በወረርሽኙ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል። ይህ ወረርሽኙ ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት ጊዜ አንስቶ በአንድ ሳምንት ውስጥ የተመዘገበ ከፍተኛው የሞት ምጣኔ ነው።
ዶ/ር ሊያ ይህም በየቀኑ በአማካይ 44 ሰዎች በወረርሽኙ ሳቢያ ህይወታቸውን እያጡ መሆኑን ያመላክታል ነው ያሉት።
አዲስ አበባ ከ1 ሚሊዮን ለሚልቁ ነዋሪዎቿ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ልትሰጥ ነው
ኢትዮጵያ በወረርሽኙ የስርጭት ደረጃ ከአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ገልጸው በተለይም ደግሞ ክትባት ያልወሰዱ ሰዎች ለወረርሽኙ የመጋለጥና የመሞት እድላቸው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ክትባት ያልወሰዱ ሰዎች ከተከተቡ ሰዎች ይልቅ፤ በወረርሽኙ ለመያዝ 4 ነጥብ 5 እጥፍ፣ በወረርሽኙ ተይዘው ሆስፒታል የመተኛት 10 እጥፍ እንዲሁም በወረርሽኙ የመሞት 11 እጥፍ አጋጣሚ ሊኖራቸው እንደሚችል ማሳያ መሆኑን ሚኒስትሯ አብራርተዋል።
ጤና ሚኒስቴር ከሰኔ ወር አጋማሽ እስከ ነሃሴ አጋማሽ 2013 ዓ.ም ባደረገው የዳሰሳ ጥናት በወረርሽኙ ለሞት የተዳረጉት ሰዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ያልተከተቡ መሆናቸውን ማረጋገጡን ተናግረዋል።
በመሆኑም ሕብረተሰቡ እንዲከተብ እና የጥንቃቄ መመሪያዎችን እንዲያከብር አሳስበዋል፡፡