ህንድ በ2023 አጋማሽ ቻይናን በመብለጥ በህዝብ ቁጥር አንደኛ ትሆናለች - ተመድ
ኒውደልሂ እስከ ሰኔ ወር ቤጂንግን በ2 ነጥብ 9 ሚሊየን ህዝብ እንደምትበልጥ ነው የተገለጸው
አሜሪካ ደግሞ በ340 ሚሊየን ህዝብ ቻይናን በመከተል 3ኛ ደረጃን ትይዛለች
ህንድ የአለማችን ባለብዙ ህዝብ ሀገር ለመሆን ተቃርባለች።
የመንግስታቱ ድርጅት በዛሬው እለት ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ ህንድ እስከ 2023 አጋማሽ ቻይናን በ2 ነጥብ 9 ሚሊየን ህዝብ በመብለጥ ቀዳሚዋ ሀገር ትሆናለች ብሏል።
በድርጅቱ የስነህዝብ ፈንድ ሪፖርት እንደሚያሳየው ኒውደልሂ በሰኔ ወር የህዝብ ቁጥሯ 1 ነጥብ 428 ቢሊየን ይደርሳል። ይህም ከቻይና በ3 ሚሊየን ገደማ የሚበልጥ ነው ይላል ሪፖርቱ።
እስከ የካቲት 2023 በተጠናቀሩ መረጃዎች ላይ ተመርኩዞ የተሰራው ጥናት አሜሪን በ340 ሚሊየን ህዝብ የአለማችን ሶስተኛ ሀገር አድርጓታል።
የስነህዝብ ባለሙያዎች ህንድ በዚህ ወር የቻይናን ደረጃ እንደምትይዝ ግምታቸውን ቢያስቀምጡም የመንግስታቱ ድርጅት የስነህዝብ ፈንድ በ2023 አጋማሽ ወይም በቀጣይ ሰኔ ወር እንደሚሆን ይገልጻል።
ይህም ሆኖ ከህንድ እና ቻይና የሚወጡ መረጃዎች መዘግየት በትክክል ወሩን ወይም ቀኑን ለማስቀመጥ አዳጋች እንደሚያደርገው ነው የጠቀሰው።
ህንድ ለመጨረሻ ጊዜ የህዝብ ቆጠራ ያደረገችው በ2011 ሲሆን፥ በ2021 ልታደርገው የነበረው ቆጠራ በኮቪድ ምክንያት ተራዝሞ እስካሁን አልተደረገም ይላል የሬውተርስ ዘገባ።
ህንድ እና ቻይና ከአለም ህዝብ ሲሶውን ቢይዙም በሀገራቱ የሚታየው የህዝብ ቁጥር እድገት እየቀነሰ መሄዱን የተመድ የስነህዝብ ፈንድ ሪፖርት ያሳያል።
ቻይና ባለፈው አመት ከስድስት አስርት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የህዝብ ቁጥሯ መቀነሱ የሚታወስ ሲሆን፥ የህንድ የህዝብ እድገት ምጣኔም ከ2011 በፊት ከነበረበት 1 ነጥብ 7 በመቶ ወደ 1 ነጥብ 2 ዝቅ ማለቱን መረጃዎች ያሳያሉ።
በህንድ የህዝብ ቁጥር ጭማሪው ፍርሃት መፍጠሩን የሚያነሱት በተመድ የስነህዝብ ፈንድ የህንድ ተወካዩ አንድሬ ወጅነር፥ “የሰዎች ፍላጎትና ምኞት እስከተሳካ ድረስ የህዝብ ቁጥር ጭማሪው የእድገት ምልክት ተደርጎ ሊወሰድ ይገባዋል እንጂ በስጋትነት መታየት የለበትም” ብለዋል።
የምድራችን የህዝብ ቁጥር በ2022 ህዳር ወር 8 ቢሊየን መድረሱ የሚታወስ ነው።