በማዕድን አውጪዎች እና ጎብኚዎች ምክንያት የመኖር ዋስትናቸው ጥያቄ ውስጥ እንደወደቀ ተገልጿል
ከምድረ ገጽ የመጥፋት አደጋ የተደቀነበት "ያኖማሚ" ብሔር።
ከ15 ሺህ ዓመታት በፊት ከእስያ እንደተሰደዱ የሚነገርላቸው "ያኖማሚ" ብሔር የመጥፋት አደጋ እንደተደቀነባቸው ተገልጿል።
በሰሜናዊ ብራዚል እና ደቡባዊ ቬንዙዌላ ተራራማ እና ውሀማ አካባቢዎች የሚኖሩት እነዚህ ያኖማሚዎች ቀስ በቀስ ዘራቸው ከምድረ ገጽ ሊጠፋ ይችላል ተብሏል።
ያኖማሚዎች በተፈጥሯቸው በሽታ የመከላከል አቅማቸው ዝቅተኛ መሆኑ ቁጥራቸው በፍጥነት እንዲመናመን እያደረገ እንደሆነ አርቲ ዘግቧል።
በተለይም ለጉብኝት እና ለማዕድን ማውጣት ስራዎች ወደ ያኖማሚዎች መኖሪያ መንደር ጎራ የሚሉ ሰዎች ወባን ጨምሮ የተለያዩ በሽታዎችን እያስተላለፉባቸው ነው ተብሏል።
የተለያዩ የዱር እንስሳትን እና አሳ በማደን የዕለት ምግባቸውን የሚያገኙት የያኖማሚ ብሔር አባላት ህልውናቸው በየጊዜው አደጋ ላይ እየወደቀ መሆኑ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
በተለይም በማዕድን ማውጣት ስራ የሚሳተፉ ሰዎች ወደ ያኖማሚ መኖሪያ አካባቢዎች መስፋፋት ለስደት እና ለሌሎች ችግሮች እየዳረጋቸው እንደሆነም የሰብዓዊ ጥበቃ ተቋማት አስታውቀዋል።
በሰሜናዊ ብራዚል እና ደቡባዊ ቬንዙዌላ የሚኖሩት ያኖማሚዎች አሁን ላይ ጠቅላላ የብሔሩ አባላት ቁጥር ከ35 ሺህ እንደማይበልጥ ተገልጿል።
የወባ በሽታ ዋነኛ ገዳይ የጤና እክል ሲሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ብቻ ከ600 በላይ ሕጻናት በዚሁ በወባ በሽታ ህይወታቸው አልፏል።
እህቴ፣ ወንድሜ፣ እናቴ ፣አባቴ ከመባባል ውጪ ሌላ መጠሪያ የሌላቸው ያኖማሚዎች በጤና ተቋማት ሲወለዱ ግን ሐኪሞች መጠሪያ ኮድ እንደሚሰጣቸው ተገልጿል።
ተመድን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት እና ሀገራት ለዚህ ብሔር ጥበቃ እንዲደረግም ተጠይቋል።