ሩሲያ ከሞስኮው ጥቃት ጀርባ አሉ ያለቻቸውን ሶስት ሀገራት ይፋ አደረገች
ጥቃቱን በማድረስ የተጠረጠሩት አራት የታጃኪስታን ዝርያ ያላቸው ግለሰቦች ክስ ተመሰርቶባቸዋል
ኤፍኤስቢ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም(ዩኬ) እና ዩክሬንን በሞስኮው ከተፈጸመው ጥቃት ጀርባ እጃቸው አለበት ብሏል።
ሩሲያ ከሞስኮው ጥቃት ጀርባ አሉ ያለቻቸውን ሶስት ሀገራት ይፋ አደረገች።
የሩሲያ የፌደራል ሴኩሪቲ ሰርቪስ( ኤፍኤስቢ) አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም(ዩኬ) እና ዩክሬንን በሞስኮው ከተፈጸመው ጥቃት ጀርባ እጃቸው አለበት ብሏል።
የኤፍኤስቢ ኃላፊ አሌክሳንደር ቦርቲኒኮቭ በትናንትናው እለት እንደተናገሩት አሜሪካ፣ ዩኬ እና ዩክሬን በሞስኮው የሙዚቃ ድግስ ላይ ከተፈጸመው እና ቢያንስ ለ133 ሰዎች ግድያ ምክንያት ከሆነው ጥቃት ጀርባ አሉ ማለታቸውን ሮይተርስ ታስን ጠቅሶ ዘግቧል።
እስላማዊ ታጣቂ ቡድን (አይኤስአይኤስ) ኃላፊነቱን በወሰደው በዚህ ጥቃት ውስጥ ዩክሬን እጇ እንደሌለበት አስተባብላለች።
የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ከዚህ ጥቃት ጋር የዩክሬን ስም መነሳቱ እንዳበሳጫቸውም ተናግረዋል።
ምዕራባውያን ሀገራት እንደገለጹት ከሆነ ጥቃቱን የፈጸመው በአፍጋኒስታን ያለው የእስላማዊ ታጣቂ ቡድን አካል የሆነው አይኤስአይኤስ-ኬ ነው።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ጥቃቱን አስመልክተው በሰጡት የመጀመሪያ መግለጫቸው ከዚህ ጥቃት ጀርባ ያሉትን እንደሚያድኑ እና እንደሚቀጡ ዝተዋል
ለጥቃቱ እስላሚክ ስቴት ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ቢገልጽም፣ ፑቲን ወደ ዩክሬን ሊያመልጡ ሲሞክሩ ተያዙ ካሏቸው አጥቂዎች ጋር ግንኙነት ያለውን ታጣቂ ቡድን ስም በይፋ አልጠቀሱም ነበር።
ፑቲን በዩክሬን በኩል መንገድ ከፍተው አጥቂዎቹን ለማስወጣት የሞከሩ ነበሩ ሲሉም ተናግረዋል።
ጥቃቱን በማድረስ የተጠረጠሩት አራት የታጃኪስታን ዝርያ ያላቸው ግለሰቦች ክስ ተመሰርቶባቸዋል።የሞስኮ መርማሪዎች ወደ ታጂኪስታን አቅንተው በተከሳሽ ቤተሰቦች ላይም ምርመራ ማካሄዳቸውም ተገልጿል።