አይኤስ አይኤስ በፓሪሱ ኦሎምፒክ ጥቃት የሚድርሱ ወጣቶችን በበይነ መረብ እየመለመለ እንደሚገኝ ተሰማ
የፓሪሱ ኦሎምፒክ ከእስራኤል እና ጋዛ ጦርነት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት አንዣቦበታል
በተያዘው አመት የደረሱ እና ለመፈጸም የታሰቡ የሽብር ጥቃቶች በ2022 ከነበረው በአራት እጥፍ ጨምሯል
በአውሮፓ የሚንቀሳቀሰው አይኤስ አይኤስ ኬ የተሰኝው የሽብር ቡድን በፓሪሱ ኦሎምፒክ ጥቃት ለማድረስ በበይነ መረብ ምልመላ እያካሄደ መሆኑ ተነግሯል፡፡
የአውሮፓ የደህንነት ባለስልጣናት በዘንድሮው ኦሎምፒክ የተደራጀ እና ነጠላ የሽብር ጥቃት በፓሪስ ሊኖር እንደሚችል በማስጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
ይህን ጥቃት በመፈጸም እና በማስተባበር ቀዳሚውን ሚና ይወጣል ተብሎ የሚጠረጠረው አይኤስ አይኤስ ኬ የተሰኝው ከዋናው የሽብር ቡድን ጋር ቀጥተና ግንኙነት ያለው ቡድን ሲሆን፤
ከሰሞኑ ጥቃቱን የሚፈጽሙ በተለይ በታዳጊ እድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎችን በበይነ መረብ ምልመላ ሲያካሂድ እንደተደረሰበት ሲኤንኤን አስነብቧል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት በሰሜን ምስራቅ እና ደቡባዊ ፈረንሳይ በኦሎምፒክ ላይ ጥቃት ለማድረስ ሲያሴሩ የነበሩ የ15 እና የ18 አመት ወጣቶች በፖሊስ መያዛቸው ተሰምቷል፡፡
ቡድኑ ምልመላውን የሚያደርገው ቲክቶክን ጨምሮ የተለያዩ ድረገጾችን በመጠቀም መሆኑ ሲገለጽ በተመሳሳይ ጊዜ በተለያዩ ቦታዎች ጥቃቶችን ለመፈጸም ዝግጅት እያደረገ ስለመሆኑ የደህንነት መረጃዎች ማመላከታቸው ነው የተሰማው፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ ለሲኤንኤን ምላሽ የሰጡት የቲክቶክ ቃል አቀባይ 98 በመቶ ሽብርተኝነትን የሚያበረታቱ እና ወጣቶችን ለመመልመል ጥረት የሚያደርጉ ገጾች መዘጋታቸውን ተናግረዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ ባለፉት ሶስት አመታት በዋናነት መቀመጫውን በማዕከላዊ እስያ እና በቱርክ አድርጓል ባሳለፍነው አመት ብቻ የቱርክ የደህነነት እና ጸጥታ ተቋማት ባደረጉት 122 ደንገተኛ አሰሳዎች 426 የሽብር ቡድኑ አባላትን በቁጥጥር ስር ማዋል ችለዋል፡፡
በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት አይኤስ አይኤስ ኬ የተሰኝው የሽብር ቡድን ስጋትነት ሲጨምር በብሪታንያ ባለፉት18 ወራት ቡድኑን ለመቀላቀል ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች ቁጥር ጭማሪ እያሳየ እንደሚገኝ የደህንነት ተቋማቶች መረጃ ጠቁሟል፡፡
የሽብር ቡድኑ ከ13 አመት ጀምሮ የሚገኙ ታዳጊዎች ላይ ማነጣጠሩ የሽብር ጥቃት ይፈጽማሉ ተብሎ የመጠርጠር አድላቸው በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ነው፡፡
በአውሮፓ ባለፉት 9 ወራት ከቡድኑ ጋር ግንኙነት አላቸው የሚባሉ 58 ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ከነዚህ መካከል 38ቱ ከ13-19 እድሜ ላይ የሚገኙ ታዳጊ እና ወጣቶች መሆናቸው ነው የተሰማው፡፡
ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ 27 የሽብር ጥቃቶች እና ሽብር ለመፈጸም ሲሸረቡ የነበሩ ሴራዎች እንደነበሩ ተደርሶበታል፡፡
በተያዘው አመት በመላው አውሮፓ የደረሱ እና ለመፈጸም የታሰቡ የሽብር ጥቃቶች ቁጥር በ2022 ከነበረው በአራት እጥፍ ጭማሪ የታየበት ነው፡፡