አቃቤህግ በፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስቴር ጥያቄ መሰረት በፓሪስ የሚገኘው የግለሰቡ መኖሪያ ቤት ላይ ፍተሻ መደረጉን ገልጿል
ፓሪስ ኦሎምፒክን ለመረበሽ በማሴር የተጠረጠረው ሩሲያዊ ግለሰብ ፈረንሳይ ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋሉን አቃቤ ህግ ገለጸ።
የ40 አመቱ ግለሰብ የተያዘው ባለፈው ቅዳሜ ሲሆን በፈረንሳይ ውስጥ አለመረጋጋት እንዲፈጠር የደህንነት መረጃዎችን ለውጭ ኃይሎች አሳልፎ በመስጠት ተጠርጥሮ ምርመራ እየተካሄደበት ነው።
ታቅዷል የተባለው ሴራ የሽብር ጥቃት አለመሆኑ ተነግሯል።
ይህ የሆነው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ሊጀመሩ ቀናት ሲቀራቸው ነው። በመጭው አርብ እለት የውድድሩ የመክፈቻ ስነ ስርአት በፈረንሳይ ፓሪስ ይካሄዳል።
አቃቤህግ በፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትር ጥያቄ መሰረት በፓሪስ የሚገኘው የግለሰቡ መኖሪያ ቤት ላይ ፍተሻ መደረጉን ገልጿል።
የጸጥታ አካላት ይህ ግለሰብ በኦሎምፒክ ውድድር ወቅት ፈረንሳይን ለመረበሽ የሩሲያን ተልእኮ መቀበሉን የሚያሳይ መረጃ መገኘቱን ቢቢሲ ሊ ፓሪሴን ጠቅሶ ዘግቧል። በጸረ-ስለላ ባለሙያዎች መርመራ እየተደረገ መሆኑ ከመገለጹ ውጭ ዝርርዝር ማብራሪያ አልተሰጠም። ግለሰቡ አሁን ላይ እስር ቤት ሆኖ ክሱን እየተጠባበቀ ይገኛል።
ይህ ወንጀል እስከ 30 አመት እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል ነው ተብሏል።
የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ጀራልድ ዳርማኒን በዚህ ሳምንት እንደተናገሩት የፈረሳይ ባለስጣናት አትሎሌቶችን፣ አሰልጣኖችን፣ ጋዜጠኞችን፣ በጎ ፈቃደኞችን፣ የደህንነት ጠባቂዎችንና የአካባቢውን ነዋሪዎች ጨምሮ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ከጨዋታው ቀደምው ፈትሸዋል።
ከእነዚህ ውስጥ 4360 ሰዎች እንዳይገቡ መከልከላቸውን እና 880 የሚሆኑት ደግሞ በውጭ ጣልቃገብነት ተጠርጥረው ጨዋታውን ለመታደም እንደማይችሉ እንደተነገራቸው ኤኤፍፒን ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል።
"እዚህ ያለነው ስፖርቱ ለሴለላ፣ ለሳይበር ጥቃት ወይም ለተችት እና ስለፈረንሳይ ለሚዋሹ ሰዎች እንዳያገለግል ለማረጋገጥ ነው" ብለዋል ዳርማኒን።
በቅርብ ወራት ውስጥ በተለይ ከጋዛ ጦርነት ጋር በተያያዘ በፈረሳይ ውስጥ ክፍፍል እና ውጥረት የሚጨምሩ ክስተቶች ተፈጥረዋል።
በሐምሌ ወር "የፈረንሳይ ወታደሮች በዩክሬን" የሚል ጽሁፍ ያለባቸው አምስት የሬሳ ሳጥኖች ኢፍል ታወር አካባቢ ተጥለው ተገኝተዋል።የፈረንሳይ ደህንት ከዚህ ክስተት ጀርባ የሩሲያ እንዳለች ያምናሉ።