በሃውቲዎች በሚሳኤል የተመታችው የብሪታንያ መርከብ “ለመስመጥ ተቃርባለች” ተባለ
የመርከቧ ሰራተኞች ከሚሳኤል ጥቃቱ በኋላ እንዲወጡ መደረጉን የብሪታንያ ማሪታይም አስተዳደር አስታውቋል
የየመኑ ቡድን በሆዴይዳህ የአሜሪካን ድሮን መትቶ መጣሉን ገልጿል
በየመኑ ሃውቲ ታጣቂ ቡድን የሚሳኤል ጥቃት የደረሰባት በብሪታንያ የተመዘገበች መርከብ “ለመስመጥ ተቃርባለች” ተባለ።
“ሩብይማር” የተባለ ተቋም ንብረት የሆነችው የጭነት መርከብ በኤደን ባህረ ሰላጤ በትናንትናው እለት በሚሳኤል ተመታለች።
የደቡብ አሜሪካዋን ቤሊዝ ሰንደቅ አላማን የምታውለበልበው መርከብ በባብ አል ማንደብ ስትጓዝ ነው የሚሳኤል ጥቃት የደረሰባት።
ከአረብ ኤምሬትስ ኮርፋካን ወደ ቡልጋሪያ እየተጓዘች የነበረችው መርከብ በሊባኖስ በሚገኝ ተቋም እንደምትተዳደር ተገልጿል።
በቤሩት የሚገኘው የመርከቧ ስራ አስኪያጅ ስለጥቃቱ እስካሁን አስተያየት ከመስጠት መቆጠቡን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
የሃውቲ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሪ ከባድ ጉዳት የደረሰባት መርከብ አሁን ላይ “ከፍተኛ የመስመጥ አደጋ አንዣቦባታል” ብለዋል።
የብሪታንያ የማሪታይም ደህንነት ተቋሙ አምብሬይም የሩብይማር መርከብ ሰራተኞች በጥቃቱ ጉዳት አልደረሰባቸውም ብሏል።
ይሁን እንጂ ፍንዳታውን ተከትሎ ሁሉም ሰራተኞች ከመርከቧ በፍጥነት እንዲወጡ መደረጉን ነው ያስታወቀው።
የብሪታንያ የማሪታንይም ንግድ አስተዳደር በበኩሉ መርከቧ ከባድ ጉዳት ስለማስተናገዷና ጉዞ አቋርጣ ሰራተኞቹ እንዲወጡ መደረጉን ባይገልጽም ጥቃቱ ስለመፈጸሙ ባወጣው መግለጫ አረጋግጧል።
ከህዳር ወር ጀምሮ ከእስራኤል፣ አሜሪካ እና ብሪታንያ ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸውን መርከቦች በቀይ ባህር አላሳልፍም ያለው የየመኑ ሃውቲ ታጣቂ ቡድን በመርከቦች ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት ቀጥሏል።
አሜሪካም በየመን የቡድኑን ይዞታዎች ላይ በአየርና ከጦር መርከቦች በሚወነጨፉ ሚሳኤሎች መምታቷን አላቋረጠችም።
ዋሽንግተን በቡድኑ የውሃ ውስጥ ድሮኖች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን መፈጸም መጀመሯንን አስታውቃለች።
የሃውቲ ታጣቂ ቡድን በሆዴይዳህ ወደብ አቅራቢያ ጥቃት ለማድረስ የተላከ የአሜሪካ ድሮንን መትቶ ማጣሉን መግለጹንም ፍራንስ 24 ዘግቧል።