ሁለቱ አካላት በግጭቱ አጀማመር ዙርያ እርስ በእርስ እየተወነጃጀሉ ሲሆን ጁበላንድ በርካታ የመንግስት ወታደሮችን መማረኳን አስታውቃለች
በትናንትናው ዕለት በሶማሊያ እና የጁባላንድ ክልላዊ መንግስት ሀይሎች መካከል ከባድ ውግያ ስለመደረጉ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል፡፡
ባለፈው ወር ባካሄደችው ምርጫ አህመድ ማዴቤን ድጋሚ የመረጠችው ጁባላንድ ከፌደራል መንግሥት ጋር ያላትን ግንኙነት ማቋረጧን ማስታወቋ ይታወሳል።
የሞቃዲሾ አስተዳደር በሶማሊያ መከላከያ ሰራዊት ጦር ሰፈር ላይ የጁባላንድ ሀይሎች ጥቃት ፈጽመዋል በሚል ከግዛቱ ሀይሎች ጋር ግጭት ውስጥ መግባቱ ተሰምቷል፡፡
የጁባላንድ ባለስልጣናት በበኩላቸው በትናንትናው እለት በራስ ካምቦኒ በፌደራል ሀይሎች የተከፈተባቸውን ጥቃት መቀልበሻቸውን አስታውቀው ለግጭቱ የሶማሊያን መንግስት ተጠያቂ አድርገዋል፡፡
ሮይተረስ ሶማሊያ ከማዕከላዊ መንግስት ጋር ያለውን ግንኙነት ካቋረጠዉ የጁባላንድ ግዛት ሃይሎች ጋር ከተቀሰቀሰው ግጭት በኋላ የፌደራል ወታደሮችን ከደቡብ ምዕራብ የታችኛው ጁባ ክልል ማስወጣት መጀመሯን ዘግቧል፡፡
ከኬንያ እና ከኢትዮጵያ ጋር የምትዋሰነው ጁባላንድ ከሶማሊያ ከፊል ራስ ገዝ አስተዳደር መካከል አንዱ ናት፡፡
አስተዳደሩ ሶስት ክልሎችን ያቀፈ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ የታችኛው ጁባ በህዝብ ብዛት ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል፡፡
የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግስት በኤክስ (ትዊተር) ይፋዊ ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ “የደም መፋሰስን ለማስቀረት እንዲሁም ለወታደሮቻችን ደህንነት ቅድሚያ በመስጠት የብሔራዊ የጸጥታ ኃይሎች ከታችኛው ጁባ እንዲወጡ ታዟል” ሲል አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም የፌደራል የጸጥታ ሀይሎች ትኩረት አማፅያንን በመዋጋት እና "የሀገሪቱን ሉዓላዊነት መጠበቅ" ላይ ብቻ እንደሚያተኩር ገልጿል፡፡
በአንጻሩ የጁባላንድ ባለስልጣናት የክልሉ ተዋጊዎች ራስ ካምቦኒ ከተማ እና በአቅራቢያው የሚገኘውን አየር ማረፊያ መያዙን እና ብዙ የፌደራል መንግስት ወታደሮች ከእሮቡ ውግያ በኋላ እጃቸውን እንደሰጡ ተናግረዋል፡፡
ሮይተርስ በሀሰን ሼክ መሀመድ የሚመራው መንግስት በህዳር ወር በጁባላንድ በተካሄደው ምርጫ የፌደራል መንግስት አልተሳተፈም በሚል የድምጽ አሰጣጡን ለማስቆም ሙከራዎችን ማድረጉን ዘግቧል፡፡
ውዝግቡ እየከረረ መምጣቱን ተከትሎ የፌደራል መንግስቱ ለሁለተኛ ጊዜ ባሸነፉት የጁባላንድ መሪ አህመድ ማዴቤ ላይ የእስር ማዘዣ ሲያወጣ አስተዳደሩ በተመሳሳይ በሀሰን ሼክ ላይ የእስር ማዘዣ እንዲወጣ አድርጓል፡፡