አሜሪካ በየመን የሁቲ የምድር ውስጥ መሳሪያ ማከማቻዎችን ደበደበች
ፔንታጎን ሁቲዎች በቀይ ባህር በሚጓዙ መርከቦች ላይ ጥቃት ለመፈጸም የሚጠቀሙባቸው መሳሪያዎች የተከማቹባቸው አምስት ስፍራዎች መመታታቸውን ገልጿል
የየመኑ ቡድን ከህዳር 2024 ጀምሮ በቀይ ባህር በሚጓዙ መርከቦች ላይ 100 የሚጠጉ ጥቃቶችን ፈጽሟል
አሜሪካ በየመን የሁቲ የምድር ውስጥ የመሳሪያ ማከማቻዎችን ደበደበች።
የሀገሪቱ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች አምስት የጦር መሳሪያ ማከማቻዎችን መምታታቸውን ፔንታጎን ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
ኢላማ የተደረጉት ስፍራዎች ሁቲዎች በቀይ ባህር በሚጓዙ መርከቦች ላይ ጥቃት ለማድረስ የሚጠቀሙባቸው መሳሪያዎች የተከማቹባቸው እንደነበሩ የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትሩ ሊዩድ ኦስቲን ተናግረዋል።
ጥቃቱ በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ትዕዛዝ መፈጸሙን ያነሱት ሚኒስትሩ፥ አሜሪካ ሃውቲዎች ህገወጥ እና ሃላፊነት የጎደለው ጥቃታቸውን ከቀጠሉ “ከባድ ዋጋ እንደሚከፍሉ” ታሳስባለች ብለዋል።
ሃውቲዎች ባለፈው ወር በመካከለኛው ምስራቅ በሚገኙ የአሜሪካ መርከቦች ላይ “ውስብስብ ጥቃት” ለማድረስ መሞከራቸውን ፔንታጎን መግለጹ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም የአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች በየመን የቡድኑ ይዞታዎች ላይ 15 የአየር ጥቃቶችን ማድረሳቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።
ፔንታጎን ትናንት የተፈጸመው ጥቃት በንጹሃን ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በጥንቃቄ መከናወኑን ገልጿል።
በመካከለኛው ምስራቅ የሚንቀሳቀሰው የአሜሪካ እዝ በአየር ድብደባው በንጹሃን ላይ ጉዳት ስለመድረሱ እስካሁን ሪፖርት አልደረሰንም ብሏል።
የየመኑ ታጣቂ ቡድን ሁቲ እስራኤል በጋዛ ጦርነት ከጀመረች አንስቶ በቀይ ባህር በሚጓዙ 100 የሚጠጉ መርከቦች ላይ ጥቃት አድርሶ ሁለት መርከቦች እንዲሰምጡ አድርጓል።
እስራኤልን ለመቃወም እና ለፍልስጤማውያን አጋርነቱን ለማሳየት በሚል በመርከቦች ላይ የሚፈጽመው የሚሳኤልና ድሮን ጥቃት የንግድ መርከቦች የጉዞ አቅጣጫን እስከማስቀየር ደርሷል።
ሁቲዎች በእስራኤል ላይ የሚሳኤልና የድሮን ጥቃት በመፈጸምም ጉዳት አድርሰዋል።
በሀምሌ ወር ከየመን ወደ እስራኤሏ ቴል አቪቭ የተላከች ድሮን የአንድ ሰው ህይወት ቀጥፋ ከ10 በላይ ማቁሰሏ ይታወሳል።
ከሁለት ሳምንት በፊትም በቴል አቪቭ አቅራቢያ በሚገኘው የቤን ጉሪን አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የባለስቲክ ሚሳኤል ጥቃት ማድረሱን ቡድኑ መግለጹ ይታወሳል።
እስራኤል ለሁለቱም ጥቃቶች በየመን የአየር ጥቃት በመፈጸም ምላሽ ሰጥታለች።
አጋሯን አሜሪካ ጨምሮ 12 ሀገራትም ከባለፈው አመት ጀምሮ የቀይ ባህር የንግድ መስመርን ከሁቲዎች ለመጠበቅ የጋራ ዘመቻ ከፍተው በየመን ተደጋጋሚ የአየር ጥቃት መፈጸማቸው አይዘነጋም።