የእስራኤል ወታደሮች ለሁለት ሳምንት ከቆዩበት አልሺፋ ሆስፒታል ወጡ
የጦርነት ቀጠና ሆኖ የሰነበተው ሆስፒታሉ መፈራረሱንና የበርካታ ሰዎች አስከሬኖችን መመልከታቸውን ፍልስጤማውያን ተናግረዋል
የእስራኤል ጦር ወታደሮቹ ከአልሲፋ ሆስፒታል ስለመውጣታቸው ማረጋገጫ አልሰጠም
የእስራኤል ወታደሮች ከአልሺፋ ሆስፒታል መውጣታቸው ተነገረ።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጋዛ ግዙፍ ወደሆነው ሆስፒታል ዛሬ ማለዳ መመለሳቸውንም አሶሼትድ ፕረስ የአይን እማኞችን ጠቅሶ ዘግቧል።
ሞሀመድ ማህዲ የተባለ ፍስጤማዊ ወደ ሆስፒታሉ ሲመለስ የተመለከተው አሳዛኝ ውድመት መሆኑን ገልጿል፤ በሆስፒታሉ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ህንጻዎች መፈራረሳቸውንና በቅጥር ግቢው ውስጥ የስድስት ሰዎችን አስከሬን መቁጠሩን ይናገራል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ያህያ አቡኡፍ በበኩሉ እስራኤል በሆስፒታሉ ውስጥ ያደረሰችው ጉዳት በቃላት የሚገለጽ አይደለም ብለዋል።
የእስራኤል ጦር በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ በቡልዶዛር ቆፍሮ የተገደሉ ሰዎችን መቅበሩንና “ሁሉንም ህይወት ያለው ነገር ማጥፋቱን”ም ነው የተናገሩት።
ድብደባውን ሽሽት ከ100 በላይ ህመምተኞች በሆስፒታሉ የሰው ሃይል ህንጻ ውስጥ ለመቆየት መገደዳቸው ተገልጿል።
የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር በሆስፒታሉ ላይ በተፈጸመው ጥቃት እስካሁን ምን ያህል ፍልስጤማውያን እንደተገደሉ አልገለጸም።
በአልሺፋ ሆስፒታል ውስጥ ለሁለት ሳምንት የዘለቀው “ታጣቂዎችን የማጽዳት ዘመቻ” ስኬታማ መሆኑን ስትገልጽ የቆየችው እስራኤልም ከሆስፒታሉ መውጣቷን አላረጋገጠችም።
እስራኤል ታጣቂዎች ምሽግ አድርገውታል ባለችው ሆስፒታል ላይ በፈጸመችው ጥቃት በርካታ የሃማስ ታጣቂዎች መደምሰሳቸውን መግለጿ ይታወሳል።
የጦር መሳሪያዎች እና ወሳኝ የስለላ መረጃዎችንም በሆስፒታሉ ውስጥ ማግኘቷን ገልጻለች።
እስራኤል በህዳር ወር ላይም በአልሺፋ ሆስፒታል ላይ ተመሳሳይ ጥቃት በመክፈት የሃማስን የምድር ውስጥ የማዛዣ ጣቢያ ማግኘቷን ይፋ ማድረጓን ሬውተርስ አስታውሷል።
ቴል አቪቭ ምንም እንኳን አልሺፋ ሆስፒታል የታጣቂዎች መደበቂያ ሆኗል የሚለውን ምክንያት ብታቀርብም ሆስፒታሉን እንዳልነበር ማድረጓና በሺዎች የሚቆጠሩ ታማሚዎችና ተፈናቃዮችን ለችግር መዳረጓ ነቀፌታ ገጥሞታል።
የአለም ጤና ድርጅትም በእስራኤል የአየርና የምድር ጥቃት በጋዛ ከሚገኙ 36 ሆስፒታሎች አሁን ላይ በመጠኑም ቢሆን አገልግሎት የሚሰጡት አስሩ ብቻ ናቸው ብሏል።