የአለም ጤና ድርጅት 9 ሺህ ታማሚዎች ከጋዛ በፍጥነት መውጣት አለባቸው አለ
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም፥ እስራኤል የጤና ሁኔታቸው አሳሳቢ የሆኑ ፍልስጤማውያን ከጋዛ እንዲወጡ ፈቃድ አሰጣጧ ፈጣን እንዲሆን እሳስበዋል
የጋዛ ጦርነት ከ26 በላይ ሆስፒታሎች ስራ እንዲያቆሙ አስገድዷል
የአለም ጤና ድርጅት 9 ሺህ ታማሚዎች ከጋዛ በፍጥነት መውጣት እንዳለባቸ ገለጸ።
አሃዙ ድርጅቱ በመጋቢት ወር መግቢያ ከጠቀሰው በአንድ ሺህ ብልጫ ያለው ነው ተብሏል።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ፥ በሺዎች የሚቆጠሩ የካንሰር ታማሚዎች፣ የኩላሊት እጥበት ማድረግ የሚገባቸውና በጦርነቱ የቆሰሉ ፍልስጤማውያን በፍጥነት ከጋዛ መውጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
“በጋዛ አሁን ላይ በዝቅተኛ አቅማቸውም ቢሆን አገልግሎት እየሰጡ ያሉት 10 ሆስፒታሎች ብቻ ናቸው” ያሉት ዶክተር ቴድሮስ፥ በሺዎች የሚቆጠሩ ህመምተኞች የጤና አገልግሎት ተነጥቀዋል ሲሉ ገልጸዋል።
የአለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በጋዛ ሰርጥ ከጦርነቱ በፊት 36 ሆስፒታሎች ነበሩ።
በእስራኤል የአየር ድብደባ 26 ሆስፒታሎች ፈራርሰውና ጉዳት ደርሶባቸው አገልግሎት ማቋረጣቸውም ተገልጿል።
እስራኤል በሰሜናዊና ደቡባዊ ጋዛ እየፈጸመችው ያለው ጥቃት መጠናከር የጋዛን የጤና ስርአት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጎዳውና በህክምና እጦት የሚሞቱ ፍልስጤማውያንን ቁጥር እንደሚጨምረው ይጠበቃል።
ሃማስን ካልደመሰስኩ ጦርነቱ አይቆምም በሚለው አቋሟ የጸናችው እስራኤል በበኩሏ የአለም ጤና ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ አለማቀፍ ተቋማት የሚያነሱትን ቅሬታ ውድቅ ታደርጋለች።
አል ሺፋን ጨምሮ በተለያዩ የጋዛ ሆስፒታሎች ላይ ጥቃት የምታደርሰውም የሃማስ ታጣቂዎች ሆስፒታሎቹን እንደ ምሽግ በመጠቀሙ መሆኑን በምክንያትነት ታነሳለች።
በጋዛ ህጻናት በረሃብ እየሞቱ ነው ያለው የአለም ጤና ድርጅት በበኩሉ፥ እስራኤል የሰብአዊ ድጋፍ የሚገባባቸውን መስመሮች ክፍት ከማድረግ ባሻገር በጦርነቱ የቆሰሉና ተከታታይ ህክምና የሚፈልጉ ፍልስጤማውያንን ከጋዛ የማስወጣቱ ጉዳይ ትኩረት ይሻል ብሏል።
ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ ከ3 ሺህ 400 በላይ ህመምተኞች እና የቆሰሉ ሰዎች በራፋህ በኩል ወጥተው ህክምና እንዲያገኙ መደረጉን ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ተናግረዋል።
“እስራኤል ታማሚዎች ከጋዛ በፍጥነት እንዲወጡ የፈቃድ አሰጣጧ ፈጣን ሊሆን ይገባዋል፤ እያንዳንዷ ቅጽበት የሰዎችን ህይወት ለመታደግ ወሳኝ ናት” ሲሉም ነው ጥሪያቸውን ያቀረቡት።
የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት በየቀኑ ከ50 እስከ 100 ፍልስጤማውያን (ከግማሽ በላዩ በካንሰር የተጠቁ) ህመምተኞች ወደ ዌስትባንክ እና ምስራቅ እየሩሳሌም ይላኩ ነበር ተብሏል።
የአለም ጤና ድርጅት እስራኤል በራፋህ የእግረኛ ጦሯን አስገብታ ጦርነት ከጀመረችም ከጦርነቱ ባሻገር በህክምና እጦት የሚሞቱ ፍልስጤማውያንን ቁጥር በእጅጉ ይጨምረዋል የሚል ስጋቱን ገልጿል።