ጆ ባይደን ሀገራቸው “በአንዲት ቻይና” እንጅ በታይዋን ነጻነት “አታምንም” ብለዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሀገራቸው አዲስ የቀዝቃዛው ጦርነት እንዲነሳ ፍላት እንደሌላት አስታውቀዋል።
የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንግ ፒንግ ከአሜሪካ አቻቸው ጆ ባይደን ጋር በበይነ መረብ ተወያይተዋል። በውይይታቸውም ታይዋን ነጻ ሀገር እንድትሆን አሜሪካ ድጋፍ እንደማታደርግም ፕሬዝዳንት ባይደን ተናግረዋል።
ዋሸንግተን፤ የቤጂንግን የመንግስት ስርዓት የመቀየር ፍላጎት እንደሌላትና ከቻይና ጋርም ግጭት ውስጥ የመግባት ምንም አይነት ፍላጎት እንደሌላት ጆ ባይደን ተናግረዋል።
የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂን ፒንግ በበኩላቸው፤ የዩክሬን ቀውስ ሀገራቸው ማየት የምትፈልግው ክስተት እንዳልሆነ ገልጸዋል።
የቻይና እና የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ባደረጉት የበይነ መረብ ውይይት ለዓለም ሰላምና መረጋጋት መረጋገጥ የበኩላቸውን ሚና መወጣት አለብን የሚል ሃሳብ ማንሳታቸውን የቻይናው ማዕከላዊ ቴሌቪዥን (ሲጂቲኤን) ዘግቧል።
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ውይይት እንደሚያደርጉ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሁዋ ቹንይንግ ቀደም ብለው ገልጸው ነበር። ፕሬዝዳንቶቹ በሁለትዮሽ እና በጋራ ጉዳዮች ላይ ያደረጉትን ውይይት ማጠናቀቃቸውም ተገልጿል።
የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂን ፒንግ ዋሸንግተን እና ቤጂንግ ዓለም አቀፍ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ለአቻቸው ጆ ባይደን “ነግረዋቸዋል” ነው የተባለው።
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች የዩክሬን እና የሩሲያ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የበይነ መረብ ውይይት ሲያደርጉ የዛሬው የመጀመሪያቸው ነው።
መሪዎቹ ሕዳር ላይ የበይነ መረብ ንግግር ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን አሁን ላይ በዩክሬን ባለው ቀውስ ዙሪያ ሀገራቱ በተቃራኒ ጎራ መቆማቸውን መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ነው።
አሜሪካ እና ቻይና የተባበሩት መንግሰታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባላት በመሆናቸው ከሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ባለፈም ለዓለም ሰላምና ጸጥታ በጋራ መስራት እንዳለባቸው ተነጋግረዋል ተብሏል።
ቤጂንግ እና ዋሸንግተን ከሰሞኑ እየተካሄደ ባለው የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ምክንያት እሰጥ አገባ ውስጥ መግባታቸው ይታወቃል።
አሜሪካ በያዝነው ሳምንት ውስጥ ቻይና በዩክሬን ጉዳይ ለሩሲያ ማንኛውንም አይነት ድጋፍ ካደረገች ዋጋ ያስከፍላታል ስትል ማስጠንቀቋም አይዘነጋም።