ሃሪ ኬን የቶተንሃም የምንግዜም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆነ
የቶተንሃም አምበሉ ኬን በሲቲ ላይ ያስቆጠራት ጎል የሊጉን መሪ አርሰናልም ጭምር የታደገች ነበረች
ኬን ለቶተንሃም በተሰለፈባቸው 416 ጨዋታዎች ላይ 267 ጎሎችን ማስቆጠር የቻለ ተጨዋች ነው
እንግሊዛዊው ሃሪ ኬን የቶተንሃም የምንግዜም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆነ፡፡
ኬን የከፍተኛ የጎል አስቆጣሪነቱን ክብር ያገኘው ክለቡ ቶተንሃም በትናንትናው እለት ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በነበረው ጨዋታ ጎል ማስቆጠሩን ተከትሎ ነው፡፡
የ29 አመቱ ኬን በሲቲ ላይ ያስቆጠራት ጎል ለክለቡ ካስቆጠራቸው ጎሎች 267ኛዋ ስትሆን፤ አስካሁን በጂሚ ግሪቭዝ ተይዞ የቆየውን የክለቡ የጎል አስቀጣሪነት ክብረወሰን እንዲያሻሽል አስችለዋለች፡፡
በተጨማሪም የቶተንሃም አምበሉ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ 200 ጎሎችን በማስቆጠር፤ 260 ጎሎችን ያስቆጠረውን አለን ሺረርን እና 208 ጎሎችን ያስቆጠረውን ዋይን ሩኒን ተከትሎ በሶስተኛ ደረጃ መቀመጥ የቻለ ድንቅ ተጨዋች ነው፡፡
ኬን ትናንት በ15ኛው ደቂቃ በማንቸስተር ሲቲ ላይ ያስቆጠራት ጎል፤ የሲቲን ግስጋሴ በመግታት ክልቡን ብቻ ሳይሆን በኤቨርተን ሽንፈት የደረሰበት የሊጉ መሪ አርሰናልም ጭምር የታደገች ነበረች ሲል ስካይ ስፖርት ዘግቧል፡፡
በጨዋታው ሲቲ ቢያሸንፍ ኖሮ ከሊጉ መሪ አርሰናል ጋር የነበረው የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ነጥብ የማውረድ እድል ነበረው፡፡ ይሁን እንጅ ሲቲ በቶተንሃም መሸነፉን ተከትሎ አርሰናል አንድ ቀሪ ጨዋታ እያለው ፤ በመካከላቸው የነበረው የአምስት ነጥብ ልዩነት አስጠብቆ ሊቀጥል ችሏል፡፡
በዚህም አርሰናል በ50 ነጥብ አንደኛ፣ ማንቸስተር ሲቲ በ45 ነጥብ ሁለተኛ፣ ማን ዩናይትድ በ42 ነጥብ ሶስተኛ፣ ኒውካስትል በ40 ነጥብ አራተኛ እንዲሁም ቶተንሃም በ39 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
ሃሪ ኬን ከቶተንሃም ጋር መጫወት የጀመረው ከ12 አመታት በፊት ገና የ18 አመት ታዳጊ ሳለ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ጎሉን ያስቆጠረው ሻምሮክ ሮቨርስ ክለብ ላይ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ኬን ለቶተንሃም በተሰለፈባቸው 416 ጨዋታዎች ላይ 267 ጎሎችን ማስቆጠር የቻለ ተጨዋተችም ነው፡፡
በጥሩ ብቃት ላይ እንዳለ የሚነገርለት ሃሪ ከይን በሊጉ ጨዋታዎች ላይ ተጨማሪ ጎሎችን በማስቆጠር፤ በሊጉ ጎል በማስቆጠር በስምንት ጎሎች ብቻ የሚበልጠውን የሀገሩ ልጅ ዋይን ሩኒን ታሪክ ይጋራል ተብሎም ይጠበቃል፡፡