ኤርትራ እና ሶማሊያ በተለያዩ መስኮች ለመስራት ስምምነት ተፈራርመዋል
ኤርትራ እና ሶማሊያ ሰላምና ጸጥታን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት ማድረጋቸውን አስታወቁ።
የኤርትራ ማስታወቂያ መስሪያ ቤት እንደገለጸው የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የሶማሊያው አቻቸው ሀሰን ሼክ መሐመድ የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት አድርገዋል፡፡ ሁከቱ መሪዎች ስምምነት ያደረጉት በሰባት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደሆነ ተገልጿል።
ሁለቱ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚስችላቸው መሆኑን የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር ይፋ አደርገዋል።
ሚኒስትሩ የማነ ገብረመስቀል እንደገለጹት ሀገራቱ በመከላከያ እና ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያም አብረው እንደሚሰሩ ማረጋገጣቸውን አስታውቀዋል፡፡
አራት ቀናትን በኤርትራ የቆዩት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በደቡባዊ እና በቀይ ባህር አካባቢዎች ጉብኝት ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በኤርትራ ስልጠና ከወሰዱ የሀራቸው ወታደሮች ጋርም መነጋገራቸው የተሰማ ሲሆን ፤ በኤርትራ የሰለጠኑት ወታደሮች ለሀገሪቱ ሰላምና ጸጥታ እንዲሁም ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ገልጸውላቸዋል ተብሏል፡፡
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና ሀሰን ሼክ መሐመድ በሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋልም ተብሏል፡፡
አስመራ እና ሞቃዲሾ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ማሳደግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መግባባት ላይ መድረሳቸውም ነው የተገለጸው፡፡
በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ እንዲሁም ትብብርና ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስር እንዲኖር ለመስራትም ሀገራቱ መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሶማሊያ አቻቸው ያደረጉት ጉብኝት ጠቃሚ እና ወቅቱን የጠበቀ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ በበኩላቸው የኤርትራ ሕዝብና መንግስት አስመራ ሲገቡ ላደረጉላቨው አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ሶማሊያ በቀድሞው ፕሬዝዳንቷ ሙሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ጊዜ ከኤርትራ ጋር ያላት ግንኑነት ጠንካራ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፤ የአዲሱ ፕሬዝዳንት የመጀመሪያ ጉብኝት ወደ አስመራ መሆንም ይህ ግንኙነት በአዲሱ ፕሬዝዳንትም እየቀጠለ መሆኑን ማሳያ ነው ሲሉ የፖለቲካ አዋቂዎች እየገለጹ ነው፡፡