ሩሲያ፤ የአውሮፓ ህብረት ለሩሲያውያን የቪዛ ማመቻቸትን የማቆም ውሳኔ “የማይረባ” ነው ስትል አወገዘች
ሩሲያ፤ ይህ ሁኔታ ለአውሮፓውያንም የበለጠ አስቸጋሪ እንደሚያደርግም አስጠንቅቃለች
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ "ይህ ለሩሲያውያን መጥፎ ዜና ነው" ብለዋል
ሩሲያ፤ የአውሮፓ ህብረት ለሩሲያውያን የቪዛ ማመቻቸትን ለማቆም የወሰነው ውሳኔ “የማይረባ” ነው ስትል አወገዘች፡፡
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሰሞኑን በቼክ ሪፐብሊኳ መዲና ፕራግ በነበራቸው ስብሰባ ሀብረቱ እንደፈረንጆቹ ከ2007 ጀምሮ ከሩሲያ ጋር የነበረውን “የቪዛ ማመቻቸት ስምምነት” ሙሉ በሙሉ ለማቆም መወሰናቸው የሚታወቅ ነው፡፡
ይህን ተከትሎ ውሳኔው ያበሳጫቸው የክሬምሊን ባለስልጣናት፤ ውሳኔውን “ምክንያታዊ ያልሆነና የማይረባ” ሲሉ ተቃውሞውታል፡፡
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "ይህ ለሩሲያውያን መጥፎ ዜና ነው፤ ቪዛ ለማግኘት ረጅም ጊዜ ይወስዳል እና የበለጠ አስቸጋሪ ይሆናል " ማለታቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ይህ ሁኔታ ለአውሮፓውያንም የበለጠ አስቸጋሪ ያደርገዋል ሲሉም ተደምጠዋል ቃል አቀባዩ፡፡
ከቀናት በፊት ከሩሲያ ወደ አጎራባች ግዛቶች የሚደረጉ የድንበር ማቋረጦች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንና ይህም ለአውሮፓ ደህንነት ስጋት መሆኑ ትኩረት ሰጥተው የተወያዩት የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮ፤ በመጨረሻም ለሩሲያውያን የሚሰጠው ቪዛ ሙሉ በሙሉ እንዲቆም ወስነዋል፡፡
አውሮፓውያን ከዚህ ውሳኔ ከመድረሳቸው በፊት፤ ሩሲያውያን ወደ አውሮፓ መግባትና ቪዛ የማግኘት ጉዳይ የተለያዩ የአውሮፓ ድምጾች የተሰሙበት አጀንዳ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡
ውሳኔውን እሮብ እለት ይፋ ያደረጉት የአውሮፓ ህብረት የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል ሳይቀር፤ ወደ አውሮፓ ህብረት የሚገቡ የሩሲያ ተጓዦች ላይ ሙሉ በሙሉ እገዳን ተግባራዊ ለማድረግ የቀረበውን ሀሳብ ሲቃወሙ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ቦሬል ቀደም ሲል በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ ሁሉም ሩሲያውያን ወደ አውሮፓ ህብረት እንዳይገቡ መከልከል "ጥሩ ሀሳብ አይደለም" ብለው ነበር፡፡
ከቦሬል በተጨማሪ እንደ ጀርመንና ፈረንሳያ ያሉ ሀገራት “ሩሲያውን ቪዛ ለመከልከል የቀረበውን ምክረ ሃሳብ” ከተቃወሙት ሀገራት እንደነበሩም ይታወቃል፡፡
እንደዛም ሆኖ፤ የአውሮፓ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተሮች ከሩሲያ ጋር ይደረግ ነበረውን የቪዛ ማመቻቸት ትብብር ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ ከመወሰን አላገዳቸውም፡፡
ውሳኔው ሩሲያን ቢያበሳጭም ፤በተደጋጋሚ እርምጃ እንዲወሰድ ስትጠይቅ ለነበረችው ዩክሬን አስደሳች ዜና ይሆናል ተብሏል፡፡