የአውሮፓ ህብረት ከሩሲያ ጋር የነበረውን “የቪዛ ማመቻቸት ስምምነት” ሙሉ በሙሉ ለማቆም ወሰነ
የአውሮፓ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ውሳኔ ለዩክሬን መልካም ዜና መሆኑ እየተነገረ ነው
ሩሲያ በአውሮፓ ላይ የደቀነቸው “የደህንነት ስጋት” ለውሳኔው ሁነኛ ምክንያት ነው ተብሏል
የአውሮፓ ህብረት ከሩሲያ ጋር የነበረውን “የቪዛ ማመቻቸት ስምምነት” ሙሉ በሙሉ ለማቆም ወሰነ፡፡
ውሳኔው የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፤ በህብረቱና እና በሩሲያ መካከል የነበረው “የቪዛ ማመቻቸት ስምምነት” ለማቆም ሚያስችላቸውን እርምጃ ለመውሰድ ላለፉት ሁለት ቀናት በቼክ ሪፐብሊክ ከመከሩ በኋላ የተደረሰ ስምምነት ነው ተብሏል፡፡
ሚኒስተሮቹ በውይይታቸው ከሩሲያ ወደ አጎራባች ግዛቶች የሚደረጉ የድንበር ማቋረጦች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ትኩረት ሰጥተው የተመለከቱት አንኳር ነጥብ እንደነበር የአውሮፓ ህብረት የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል አስታውቋል፡፡
ሚኒስትሮቹ የድንበር ማቋረቱ ሁኔታ በአውሮፓ ከፍተኛ የሆነ ደህንነት ስጋት መደቀኑን በተመለከተ መወያየታቸውም ተገልጿል፡፡
በዚህም መሰረት የአውሮፓ ህብረት ከሩሲያ ጋር የነበረውን “የቪዛ ማመቻቸት ስምምነት” ሙሉ በሙሉ ለማቆም መወሰኑ ጆሴፕ ቦሬል ከደቂቃዎች በፊት በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ ይፋ አድርገዋል፡፡
አውሮፓውያን ከዚህ ውሳኔ ከመድረሳቸው በፊት ፤የሩሲያውያን ወደ አውሮፓ መግባትና ቪዛ የማግኘት ጉዳይ ፤ የተለያዩ የአውሮፓ ድምጾች የተሰሙበት አጀንዳ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡
ውሳኔው ይፋ ያደረጉት የአውሮፓ ህብረት የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል ሳይቀር፤ ወደ አውሮፓ ህብረት የሚገቡ የሩሲያ ተጓዦች ላይ ሙሉ በሙሉ እገዳን ተግባራዊ ለማድረግ የቀረበውን ሀሳብ ሲቃወሙ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ቦሬል ከቀናት በፊት በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ ሁሉም ሩሲያውያን ወደ አውሮፓ ህብረት እንዳይገቡ መከልከል "ጥሩ ሀሳብ አይደለም" ብለው ነበር፡፡
ከቦሬል በተጨማሪ እንደ ጀርመንና ፈረንሳያ ያሉ ሀገራት “ሩሲያውን ቪዛ ለመከልከል የቀረበውን ምክረ ሃሳብ” ከተቃወሙት ሀገራት እንደነበሩም ይታወቃል፡፡
ያም ሆኖ፤ ላለፉት ሁለት ቀናት (ማክሰኞና እሮብ) በቼክ ሪፐብሊኳ መዲና ፕራግ ለውይይት ተቀምጠው ነበሩት የአውሮፓ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተሮች ከሩሲያ ጋር ይደረግ ነበረውን የቪዛ ማመቻቸት ትብብር ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ መወሰናቸው ተግልጿል፡፡
ውሳኔው በተደጋጋሚ እርምጃ እንዲወሰድ ስትጠይቅ ለነበረችው ዩክሬን አስደሳች እንዲሁም ለክሬምሊን ሰዎች አሳዛኝ ዜና ይሆናልም ነው የተባለው፡፡