በቤተ ሙከራ የተቀነባበሩ ምግቦች በመጪዎቹ ሁለት አመታት ለብሪታንያ ገበያ ሊቀርቡ ነው
ስጋ ፣ የወተት ተዋጽዖ ፣ ስኳር እና ሌሎችም በቤተ ሙከራ የተቀነባበሩ ምርቶች ጥራት ግምገማ እየተጠናቀቀ ነው ተብሏል

ሲንጋፖር ፣ አሜሪካ እና እስራኤል የቤተ ሙከራ ምግቦችን ለምግብነት በማዋል ቀዳሚዎቹ ናቸው
በብሪታንያ በቤተ ሙከራ የተቀነባበሩ ምግቦች በሚቀጥሉት ሁለት አመታት ውስጥ ለገበያ እንዲቀርብ ፈቃድ ልትሰጥ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
የሀገሪቱ የምግብ ደረጃዎች ኤጄንሲ በቤተ ሙከራ ውስጥ የሚመረት ሥጋ፣ የወተት ተዋጽኦ ፣ ስኳር እና ሌሎችም ምርቶች ለሰው ልጅ ፍጆታ እንዲውል ከተጠበቀው ጊዜ ቀድሞ ፈቃዱ እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡
በትናንሽ ኬሚካላዊ ተክሎች ውስጥ ከሚገኙ ሴሎች ውስጥ የሚበቅሉት የቤተ ሙከራ ምግቦችን በማቀነባበር ብሪታንያ ከቀዳሚዎቹ ሀገራት ተርታ የምትመደብ ቢሆንም በተለያዩ ህጎች እና ቁጥጥሮች ምክንያት ምርቶቹን ወደ ገበያ ማቅረብ አልቻለችም፡፡
ሆኖም ለውሻ ምግብነት የሚውል በፋብሪካ የተመረተ የስጋ ውጤት ባለፈው ወር ለመጀመሪያ ጊዜ በብሪታንያ ለገበያ ቀርቧል፡፡
እ.ኤ.አ. በ 2020 ሲንጋፖር በሴል የሚመረተውን ስጋ ለሰው ልጅ ፍጆታ እንዲሸጥ ፍቃድ የሰጠች የመጀመሪያዋ ሀገር ስትሆን አሜሪካ ከሶስት አመት በኋላ እና እስራኤል ባለፈው አመት በመፍቀድ በደረጃ ይገኛሉ።
የላብራቶሪ የተቀነባበሩ ምግቦች ተፈጥሯዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ ለምግብነት መዋል እንደሚችሉ የሚናገሩ ተደጋጋሚ የጥናት ውጤቶች ቢኖሩም ለሰው ልጅ ምግብነት እንዳይውሉ የከለከሉም አልጠፉም፡፡
ጣሊያን እና የአሜሪካዎቹ አላባማ እና ፍሎሪዳ ግዛቶች የላብራቶሪ ምግቦች እንዳይሸጡ እገዳ ከጣሉት መካከል ናቸው፡፡
የብሪታንያ የምግብ ደረጃዎች ኤጄንሲ ከከፍተኛ የቴክኖሎጂ የምግብ ድርጅቶች ባለሙያዎች እና ተመራማሪዎች ጋር በመተባበር የምግብ ጥራት ደረጃዎችን ለመወሰን አዲስ ደንቦችን እያዘጋጀ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
በመጪዎቹ ሁለት አመታት የስጋ እና የወተት ተዋጽኦ ምግቦችን ጥራት እና ደረጃ በመወሰን ለገበያ የሚቀርቡበትን ሂደት ለማጠናቀቅ ተቆጣጣሪ አካሉ እየሰራ እንደሚገኝ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የለንደን ኢምፔሪያል ኮሌጅ ባልደረባ አሊስ ግርሀም የተቀነባበሩ ምግቦችን ለማምረት የሚፈልጉት ሀይል በተፈጥሮ ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ተናግረው ከጤናም አንጻር የተፈጥሯዊውን ያህል አዋጭ እንዳልሆኑ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በቤተ ሙከራ ከሚቀነባበሩ ምግቦች ባለፈ ተመራማሪዎች ኩላሊት እና ልብን ጨምሮ ሌሎች የሰውነት ክፍሎችን ለመፍጠር በሙከራ ላይ ናቸው፡፡