በቤተሙከራ የሚበለጽግ ስጋ ከባቢ አየርን ይበክላል - ጥናት
የሆላንድ ተመራማሪዎች የቤተሙከራው ስጋ ከእንሰሳት ስጋ 25 በመቶ በበለጠ አየርን ይበክላል ብለዋል
በቤተሙከራ የሚሰራ ስጋ ከፍተኛ የካርበን ዳይ ኦክሳይድ እንደሚለቅ በጥናቱ ተረጋግጧል
የሰው ልጅ ስጋን ከእንሰሳት ለማግኘት በሚያደርገው ጥረት ውስጥ የከባቢ አየር ብክለት እንደሚፈጠር ይነገራል።
ለእንስሳቱ ውሃ፣ ምግብ እና መጠለያ ለማቅረብ በሚካሄድ እንስቅስቃሴ ካርበን ዳይ ኦክሳይድ በከፍተኛ ደረጃ ይለቀቃል ነው የሚሉት ተመራማሪዎች።
ይህንንም ለማስቀረት የከብቶችን ህዋሳት በመውሰድ በቤተሙከራ ስጋ ማምረት ከተጀመረ ሰነባብቷል።
በተለይ የብሪታንያ ተመራማሪዎች በቤተሙከራ የበለጸገውን ስጋ በስፋት አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ ሰፊ ምርምር እያደረጉ መሆኑን ነው ዴይሊ ሜል ያስነበበርው።
የቤተሙከራው ስጋ የእርድ ከብቶችን ከማርባት የሚገላግልና የበካይ ጋዝ ልቀትን የሚቀንስ ነው ተብሎ ቢታመንም የሆላንድ ተመራማሪዎች ያደረጉት ጥናት ግን ተቃራኒውን አመላክቷል።
በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ድጋፍ የተደረገው ጥናት የቤተሙከራው ስጋ ከተፈጥሯዊው ስጋ 25 በመቶ የከፋ የአየር ንብረትን ይበክላል ይላል።
በቤተሙከራ ስጋ ለማምረት ግብአት የሚሆኑ ኬሚካሎች እና የሚፈልገው የሃይል ፍጆታም ብክለቱን ይፈጥራል ብሏል ጥናቱ።
ከእንሰሳት ተዋጽኦ ይልቅ አትክልትና ፍራፌዎች ላይ ያተኮረ አመጋገብን ለማሳደግ የሚሰራው “ጉድ ፉድ ኢንስቲትዩት” ግን ጥናቱ ገና በባለሙያዎች ያልተገመገመና ያስቀመጣቸው ግምታዊ መረጃዎችም ሊለወጡ የሚችሉ ናቸው በሚል ተቃውሞውን ገልጿል።
ባለሙያዎች እንደሚሉት በቀጣይ አስር አመታት በበለጸጉት ሀገራይ በላብራቶሪ የሚመረተው ስጋ የክበቶችን ስጋ እንደሚተካ ይጠበቃል።
ለዚህም ኩባንያዎች በዘርፉ ቢሊየን ዶላሮችን ወጪ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል ነው የተባለው።