ኢሰመኮ በመጠለያ ጣቢያዎች የሚወሰዱ ማናቸውም የሕግ ማስከበር እርምጃዎች ተገቢውን የሕግ ሂደት እንዲከተሉ አሳሰበ
እርምጃዎቹ በመጠለያዎቹ ያሉ ተፈናቃዮችን ሁኔታ ታሳቢ ያደረጉ መሆን አለባቸውም ብሏል
ኮሚሽኑ በመጠለያዎቹ ይገኛሉ ተብለው የሚታሰቡ ተጠርጣሪዎችን የመያዝ እርምጃዎች ተገቢውን የሕግ ሂደት እንዲከተሉም ነው ያሳሰበው
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በመጠለያ ጣቢያዎች የሚወሰዱ ማናቸውም የሕግ ማስከበር እርምጃዎች ተገቢውን የሕግ ሂደት የተከተሉ እንዲሆኑ አሳሰበ፡፡
ኢሰመኮ ከግንቦት 16 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በትግራይ ክልል፣ ሽሬ ከተማ ከሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚገኙባቸው የመጠለያ ካምፖች ውስጥ በጸጥታ ኃይሎች የተወሰዱ በርካታ ተፈናቃዮች ስላሉበት ሁኔታ ክትትል በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቋል።
መጠለያዎቹ መደበኛ መኖሪያ ቦታቸው ያለውን የደኅንነት ስጋት ሸሽተው የመጡ ሰዎች ብቸኛ የደህንነት ቦታዎች ናቸው ያለው ኮሚሽኑ በመጠለያዎቹ ያለው የሰብአዊ አቅርቦት ፍላጎት አሁንም ከፍተኛ መሆኑ እንደሚታወቅ ገልጿል።
በመሆኑም መጠለያዎቹ የሚወሰዱ ማናቸውም የሕግ ማስከበርም ሆኑ በመጠለያዎቹ ይገኛሉ ተብለው የሚታሰቡ ተጠርጣሪዎችን የመያዝ እርምጃዎች ተገቢውን የሕግ ሂደት የተከተሉ ሊሆኑ እንደሚገባ ነው ያሳሰበው፡፡
እርምጃዎቹ በመጠለያዎቹ ያሉ ተፈናቃዮችን ሁኔታ ታሳቢ ያደረጉ መሆን አለባቸውም ብሏል።
ኢሰመኮ የሲቪል ሰዎችን ደኅንነት እና ሰላም አደጋ ላይ የሚጥሉ ማናቸውንም አይነት ተግባራት የሚያወግዝ መሆኑን የገለጸም ሲሆን አፋጣኝ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ሲል ነው በአጽንኦት ያሳሰበው።
የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና መጠለያ ቦታዎቻቸው በማንኛውም ጊዜ ቢሆን ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባም አስታውሷል፡፡
በትግራይ ባጋጠመው ግጭት እና በህግ ማስከበር ዘመቻው ምክንያት በርካቶች የመኖሪያ ቀያቸውን ለቀው ተፈናቅለዋል፡፡
በመቀሌ፣ ሽሬ እና በሌሎችም ከተሞች ተጠልለውም ይገኛሉ፡፡