በአቶ መለስ ስም “የተሰየመን ተቋም መምራት ለእኔ እንደ ውርደት የሚቆጠር አይደለም”- አወሉ አብዲ
“ከተልዕኮው እንጂ ከስያሜው ብዙም አጀንዳ የለኝም”
“ሹመቱ የ’ዲሞሽንና ፕሮሞሽን‘ ጉዳይ ሳይሆን የድርጅታዊ ተልዕኮ ጉዳይ ነው”
“በእርሳቸው [አቶ መለስ] ስም የተሰመየን ተቋም መምራት ለእኔ እንደ ውርደት ወይ እንደ ሃፍረት የሚቆጠር አይደለም”
የብልጽግና ፓርቲ የህዝብና የውጭ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ አወሉ አብዲ የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ፕሬዝዳንት ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር የስልክ ቆይታ አድርገዋል፡፡
ሹመቱ ከአሁን ቀደም እንደሚደረገው የአመራር ምደባ ሁሉ መደረጉን የገለጹት አቶ አወሉ በጸጋ ስለመቀበላቸው ተናግረዋል፡፡
ከአሁን ቀደም በተመሳሳይ መልኩ አካዳሚውን እንዲመሩ ሹመት ተሰጥቷቸው የነበሩት የቀድሞው የአማራ ክልል ብልጽግና ጽ/ቤት ኃላፊ ዮሐንስ ቧያለው “ተቋሙ አሁን ባለው ስያሜ እና ብራንድ ለማገልገል ዝግጁ አለመሆኔን አስታውቄያለሁ” በሚል ሹመቱን ለመቀበል እንደሚቸገሩ መግለጻቸውን በማስታወስ እሳቸው [አቶ አወሉ] ሹመቱን እንዴት በጸጋ ሊቀበሉት እንደቻሉ አል ዐይን ላቀረበላቸው ጥያቄም “የተልዕኮ ልዩነት እንጂ እንደሌሎቹ ድርጅታዊ ተልዕኮዎች ሁሉ ይኼም ሹመት ነው፤ የሃገር የአመራር ቦታ ነው በጸጋ ነው የተቀበልኩት” ሲሉ መልሰዋል፡፡
“ዋናው ነገር ተቋሙ የሚጠራበት ስም አይደለም፤ አቶ መለስም ቢሆኑ ብዙ ስራ የሰሩ ሰው ናቸው የዚህ ሃገር መሪ ነበሩ በዛው ልክ ችግሮችና የሚስተካከሉ የጎደሉ ነገሮች ቢኖሩም ሃገር መሪ ነበሩ፤ በእርሳቸው ስም የተሰመየን ተቋም መምራት ለእኔ እንደ ውርደት ወይ እንደ ሃፍረት የሚቆጠር አይደለም” ሲሉም ነው ያስቀመጡት፡፡
“ዋናው ነገር አካዳሚው ምን ይሰራል? አመራር እንዴት ያፈራል? ነው እንደሚታሰበው ጠንካራ አመራሮችን ያፈራል ወይ ነው?” ሲሉም ያክላሉ፡፡
“ጠንካራ የብልጽግና አመራር የማፍራት እንጂ የስያሜ ጉዳይ አይደለም” ያሉም ሲሆን “ከተልዕኮው እንጂ ከስያሜው ብዙም አጀንዳ የለኝም” በሚልም ነው የሚናገሩት፡፡
ወደ አካዳሚ አመራርነት የሄዱበት ሁኔታ ተሽረው ወይስ ተሾመው (በዲሞሽን ወይስ በፕሮሞሽን) እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄም “ጉዳዩ የድርጅታዊ ተልዕኮ እንጂ የዲሞሽን እና ፕሮሞሽን ጉዳይ አይደለም” ሲሉ መልሰዋል፡፡
የአካዳሚው ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሆነና ሹመቱም በእሳቸው እንደሚሰጥ ነው የገለጹት፡፡
“በድርጅት አሰራር ውስጥ የተሰጠህን ተልዕኮ መወጣት [የግድ] ነው፤ ለምን ዘበኛ አይሆንም የዘበኝነት ስራ ለድርጅቱ ለፓርቲው ይጠቅማል ከተባለ ያንን ተቀብለህ መፈጸም ነው እከሌ እከሌ የምትለው አይደለም” ሲሉም የሹመቱን ድርጅታዊ ተልዕኮነት ያስቀምጣሉ፡፡
አቶ አወሉ “ተልዕኮው ህዝቡን ምን ያህል ይጠቅማል በተለይ አሁን ካለንበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር የአመራሩ ሚና ምንድነው? አመራሩ ምን ሊያደርግ ይገባዋል? እንዴትስ እናበቃዋለን? የሚለውን ነገር እንጂ የዲሞሽንና ፕሮሞሽን ጉዳይ አይደለም ምክንያቱም እዚህም ሚኒስትር እዛም ሚኒስትር ነው እዛ የኮሙኒኬሽን ሃላፊ ነበርኩ አሁን ደግሞ የአመራር አቅም ግንባታ ላይ ነው የምሰራው የተልዕኮ ልዩነት ነው እንጂ ሁለቱም ተልዕኮዎች ናቸው” ሲሉም ይናገራሉ፡፡
“አካዳሚው ከአሁን ቀደም አንጋፋ በሚባሉ የፖለቲካ ሰዎች መመራቱን የገለጹም ሲሆን ዋና ስራዬ ተቋሙን ሪፎርም ማድረግ ሪፎርም አድርገን ከህዝብና ከመንግስት ፍላጎት አንጻር ከአጠቃላይ አሁን ካለንበት ሃገራዊ ሁኔታ አንጻር ተልዕኮውን ሊወጣ በሚችል መልኩ ሪፎርም ማድረግ ነው” ብለዋል፡፡
ተቋሙ በህዝብ ዘንድ ያለውን ስም በማሻሻል ተቀባይነቱን በማሳደግ በሃገሪቱ የብልጽግና ጉዞ ውስጥ የራሱን አሻራ እንዲያኖር ለማድረግ በሚያስችል መልኩ በአዲስ እንደሚደራጅም ገልጸዋል፡፡
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ አቶ አወሉን ተክቶ በብልጽግና ቃል አቀባይነት የተሾመ ስለመኖሩ የታወቀ ነገር የለም፡፡