ሽምግልናው በመንግስት አነሳሽነት የተጀመረ ነው መባሉ እንዳሳዘናቸው የሃገር ሽማግሌዎች ገለጹ
ጥረታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉና ሌሎች ክልሎችና አካባቢዎች በመድረስ ሀገራዊ መግባባትን ለማጎልበት እንደሚሰሩም አስታወቀዋል
ሂደቱን በማሳነስና አንድ ወገን አጥብቆ እንደሻው በማስመሰል መራገቡ ጥረቱን ለማደናቀፍ እንደሆነም ገልጸዋል
ሽምግልናው በመንግስት አነሳሽነት የተጀመረ ነው መባሉ እንዳሳዘናቸው የሃገር ሽማግሌዎች ገለጹ
ወደ መቀሌ ያመሩት በመንግስት ወይም በብልጽግና ፓርቲ አነሳሽነት ነው መባሉ እንዳሳዘናቸው የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት አባላት አስታወቁ፡፡
በፌዴራል እና በትግራይ ክልል መንግስት መካከል ያለው ችግር በሠከነ ውይይት ሊፈታ ይገባል በሚል መነሻ ከሰሞኑ ወደ መቀሌ ማምራታቸውን ያስታወቁት የሃይማኖት አባቶቹ እና የመማክርቱ አባላት የሽምግልናውን ሂደት በማሳነስ በመንግስት ወይም በብልጽግና ፓርቲ አነሳሽነት እንደተጀመረና ሽማግሌዎቹም ተላላኪ እንደሆኑ እንዲሁም አንድ ወገን አጥብቆ እንደሻው በማስመሰል በማህበራዊ ሚዲያዎች በስፋት መራገቡ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል፡፡
ይህ በራስ ተነሳሽነት የተጀመረውን ሂደት በከፍተኛ ቁርጠኝነትና ጥንቃቄ ልንሰራበት እንደሚገባ የተማርንበትም ነው ያሉት የሃይማኖት አባቶቹ እና የመማክርቱ አባላት አንዳንድ ሚዲያዎች ጭምር እያደረጉት ያለው አፍራሽና አሉታዊ እንቅስቃሴ እንዲታረም እና ኃላፊነት በጎደለው መልኩ የሚጽፉ ወገኖችም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል፡፡
የትግራይ ክልል መንግስት ላሳየው አክብሮትና ዝግጁነት ያመሰገኑም ሲሆን ሂደቱ ቀደም ቢል ጥሩ ይሆን እንደነበር አስገንዝቧልም ብለዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ ሠኔ 9 ቀን 2012 ዓ/ም ምሽት 4፡00 ከመቀሌ ወደ አዲስ አበባ የገባው የልዑካን ቡድኑ በማግስቱ ሠኔ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ከቀኑ 9፡00 ሰአት ላይ ከፌዴራል መንግስት የሥራ ኃላፊዎች እና ከብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ጋር መወያየቱንም ገልጿል፡፡
ሽምግልናው ሙሉ እውቅናና ይሁንታ አግኝቷል ያለም ሲሆን ሂደቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ሌሎች ክልሎችና አካባቢዎችን በስፋት በመድረስ ሀገራዊ መግባባቱን የሚያጎለብቱ ሥራዎች በስፋት እንደሚሠሩም ነው ሂደቱን በማስመልከት በጉባዔው ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ባሰፈረው ጽሁፍ ያስታወቀው፡፡