የቤላሩስ መሪ ዩክሬን ሚሳኤል እንደተኮሰችባቸው ገለጹ
ቤላሩስ ሚሳዔሎቹን “ፓንትሲር” በተባለ የአየር መከላከያ ስርዓት ተመትተው እንዲከሽፉ አድርጌያለሁ ብላለች
ሩሲያ ቤላሩስን ኒውክሌር እንደምታስታጥቅ ገልጻለች
የቤላሩስ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሸንኮቭ ዩክሬን በሀገራቸው ላይ የሚሳኤል ጥቃት መሰንዘሯን አስታወቁ።
ፕሬዝዳቱ ፤ ከሩሲያ ጋር ውጊያ ውስጥ ያለችው ዩክሬን ወደ ቤላሩስ ሚሳኤል መተኮሷን የሀገራቸው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡
ሆኖም ግን ዩክሬን ወታደራዊ ኢላማዎችን ለመምታት ያስወነጨፈቻቸው ሚሳዔሎች አየር ላይ እንዳሉ በሀገሪቱ ጦር ተመትተው መክሸፋቸውን ፐሬዝዳንት ሉካሽንኮ አስተቀወቀዋል።
ከዩክሬን የተተኮሱ ሚሳዔሎችን “ፓንትሲር” በተባለ የአየር መከላከያ ስርዓት ተመትተው እንዲከሽፉ መደረጋቸውንም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
ቤላሩስ አሁን ላይ ከሩሲያ ጎን በመቆም አጋርነቷን እያሳየች ሲሆን ዩክሬን እና አጋሮቿ “ጸብ አጫሪ” በሚል እየፈረጇት ነው፡፡
የቀድሞዋ የሶቪየት ህብረት አባል ሀገር የነበረችው ቤላሩስ ከዩክሬን ጋር ባለው ጦርነት ከሩሲያ ጎን ከቆሙ ሀገራት መካከል ብቸኛዋ ናት፡፡
ከቤላሩስ ውጪ ሁሉም የቀድሞዎቹ የሶቪየት ህብረት አባል ሀገራት ከሩሲያ በተቃራኒ ወይም ከምዕራባዊያን ጎን ተሰልፈው የተለያዩ እርምጃዎችን የወሰዱ ሲሆን የምዕራባዊያንን ማዕቀብንም በማስፈጸም ላይ ናቸው።
የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶ ጦሩን በቤላሩስ ድንበሮች አቅራቢያ ማድረጉ ምቾት የነሳቸው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አልክሳንደር ሉካሸንኮ ሞስኮን በመጎብነጠት ላይ ናቸው።
ፕሬዝዳንቱ በሞስኮ ቆይታቸው ከሩሲያ አቻቸው ጋር በኔቶ ጦር ጉዳይ የተወያዩ ሲሆን ከውይይቱ በኋላም ሩሲያ ለቤላሩስ ኑክሌር አረር ለማስታጠቅ መወሰኗን ገልጻለች።
ሩሲያ ኢስካንዳር-ኤም የተሰኘውን ኑክሌር ተሸካሚ ሚሳኤል በጥቂት ወራት ውስጥ ለቤላሩስ እንደምታስታጥቅ ፕሬዝዳንት ፑቲን ተናግረዋል።