ከአርብ ዕለት ጀምሮ ሉቲኒያ የሩሲያን ነዳጅ አልተጠቀመችም ተብሏል
ሩሲያ ወዳጅ ያልሆኑ ሀገራት ጋዝን በሩብል እንዲገዙ አስገዳጅ ውሳኔ ከወሰነች በኋላ የቀድሞ ሶቬት ህብረት አባል ሀገር የሆነችው ሉታኒያ ጋዝ መግዛት ማቆሟን ገልጻለች፡፡
ሉታኒያ ከሩሲያ ጋዝ መግዛት ያቆመች የመጀመሪያዋ የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገርም ሆናለች ተብሏል፡፡ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሀገራቸው ከፈረንጆቹ ሚያዚያ አንድ ቀን በኋላ ጋዝ የምትሸጠው በራሷ የመገበያያ ገንዘብ “ሩብል” እንዲሆን መወሰናቸውን ተከትሎ ሉታኒያ ጋዝ ከሩሲያ እንደማትገዛ አስታውቃለች፡፡
ቭላድሚር ፑቲን ሀገራቸው ከዚህ በኋላ ወዳጅ ላልሆኑ ሀገራት ጋዝን የምትሸጠው በሩብል እንዲሆን የወሰኑትን ውሳኔም ሊታኒያ አጣጥላዋለች ነው የተባለው፡፡ ሩሲያ ደግሞ የጋዝ ሽያጩ በሩብል እንዲሆን የቀረበው ሃሳብ ቶሎ ተግባራዊ እንዲሆን ማስታወቋ ይታወሳል፡፡ ይህንን ተግባራዊ የተደረገ የጋዝ ሽያጭን የተቃወመችው ሉታኒያ ታዲያ ውሳኔው “ትርጉም አልባ ነው” ብላለች፡፡
የሉታኒያ የኢነርጅ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ከዚህ በኋላ ከሩሲያ ጋዝ የመግዛት ፍላጎትና ዕቅድ እንደሌለው አስታውቋል፡፡ ሉታኒያ ከዚህ በፊት የጋዝ ፍላጎቷን ታሳካ የነበረው በሩሲያው የጋዝ አቅራቢ ጋዝፕሮም የነበረ ቢሆንም አሁን ግን “ፍላጎት የለኝም” እያለች ነው፡፡
የሉቲኒያ የኢነርጂ ሚኒስትር ዳይኒዩስ ክሬይቭስ ጋዝን ከሩሲያ ላለመግዛት የተወሰነው ውሳኔ ከረጅም ጊዜ በፊት የተጀመረ፤ በደንብ የታሰበበት፤ ቅደም ተከተልን የጠበቀ የኢነርጂ ፖሊሲ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ሚኒስትሩ ውሳኔው ወቅታዊ የመሰረተ ልማት ውሳኔ እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡ ምንም እንኳን ሚኒስትሩ ይህንን ቢሉም ውሳኔው ግን ከሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በኋላ የመጣ እንደሆነ ግን ተገማች ሆኗል፡፡
ሩሲያ ነዳጅን “በሩብል ብቻ ነው የምሸጠው”` ካለችበት ዕለት ጀምሮ የሉቲኒያ የጋዝ ስርጭት ካለሩሲያ ምርት እየቀጠለ ነው ሲል ሚኒስቴሩ በድረ ገጹ ላይ አስፍሯል፡፡