ሩሲያ በኪቭ አካባቢ የምታደርገውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለመቀነስ ቃል ገባች
በረቂቅ የስምምነት ሃሳብ ላይ ስምምነት ከተደረሰ በኋላ የሁለቱ ሃገራት መሪዎች በግንባር ተገናኝተው ሊነጋገሩ እንደሚችሉ ተገልጿል
በሩሲያ እና ዩክሬን ልዑካን መካከል በአንካራ የተካሄደው ውይይት መጀመሪያ ዙር ተጠናቋል
በሩሲያ እና ዩክሬን ዲፕሎማቶች መካከል በቱርክ አንካራ የተካሄደው ድርድር የመጀመሪያ ዙር ተጠናቀቀ፡፡
ድርድሩ ለ2 ቀናት የሚካሄድ ሲሆን ነገ ረቡዕም ቤሺክታሽ ተብሎ በሚጠራው የአንካራ አካባቢ በሚገኘው የኦቶማን ቱርክ ዶልማባህ ቤተመንግስት መካሄዱ ይቀጥላል፡፡
ከድርድሩ ቀደም ብለው ትናንት ሰኞ አንካራ የገቡት ተደራዳሪዎቹም በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት ሊቆም በሚችልባቸው መንገዶች ዙሪያ መክረዋል፡፡ ሆኖም ከስምምነት ላይ አልደረሱም፡፡
በምክክሩ ሩሲያዊው ቱጃር ሮማን አብራሞቪች መገኘታቸውም ተሰምቷል፡፡ የቼልሲው ባለቤት አብራሞቪች በእንግሊዝ መንግስት በተጣለባቸው ከባድ ማዕቀብ ምክንያት ክለባቸውን ለመሸጥ በማስማማት ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
የድርድሩ ተሳታፊዎች ከድርድሩ በኋላ የተናጠል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ድርድሩ በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታትም ይቀጥላል ያሉት የፕሬዝዳንት ቬሎዶሚር ዜሌኒስኪ አማካሪ የሆኑት የዩክሬን ተደራዳሪዎች ሃገራቸው የደህንነት ዋስትና የምታገኝ ከሆነ ገለልተኛ ለመሆን እንደምትስማማም ገልጸዋል፤ በስምምነቱ ላይ ህዝበ ውሳኔ እንደሚያስፈልግ በመጠቆም።
የክሬሚያ ጉዳይ ለብቻው እንደሚታይ የገለጹም ሲሆን ቱርክን ጨምሮ ለወደፊት ሰላማችን ዋስትና ናቸው ያሏቸውን ስምንት ሃገራት ዘርዝረው አስቀምጠዋል፡፡ ሩሲያ ክሬሚያን በ2014 ወደ ግዛቷ መጠቅለሏ ይታወሳል፡፡
የሩሲያ ተደራዳሪዎች በበኩላቸው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና ዜሌንስኪ በረቂቅ የስምምነት ሃሳቡ ላይ ስምምነት ከተደረሰ በኋላ በግንባር ሊገናኙ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ ይህ የዩክሬን ተደራዳሪዎች በግለጫቸው የጠቀሱት ነገርም ነው፡፡
ሆኖም መሪዎቹ የሚገናኙት ተደራዳሪዎቹ በሚያዘጋጁት ረቂቅ የስምምነት ሃሳብ ላይ ከተስማሙ እና በሃገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከተፈረመ በኋላ ነው እንደ ተደራዳሪዎቹ ገለጻ፡፡
ደርድሩን ተከትሎ ሩሲያ በኪቭ እና በሰሜናዊ ዩክሬን ቼርኒሂቭ አካባቢ የምታደርገውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለመቀነስ ቃል ገብታለች፡፡
የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶግሉ ድርድሩ ተስፋ ሰጭ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
በዚህ መካከል ግን ጦርነቱ ቀጥሏል፡፡ የዩክሬን ወታደሮችም በሩሲያ ጦር የተያዙ የኪቭ መሬቶችን መልሶ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ውጊያ በማካሄድ ላይ ናቸው፡፡