የዩክሬን መሪ ከቱርክ ፕሬዝዳንት እና ከተመድ ዋና ጸሐፊ ጋር በኪቭ ሊገናኙ ነው
ዜለንስኪ፣ ኤርዶጋን እና ጉቴሬዝ በዚህ ሳምንት በኪቭ ይገናኛሉ ተብሏል
የዛፓሪዢያ ኒውክሌር ጣቢያ ጥቃት ጉዳይ ሩሲያ እና ዩክሬንን እያነታረከ ይገኛል
የዩክሬን መሪ ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ከቱርክ ፕሬዝዳንት እና ከተመድ ዋና ጸሐፊ ጋር በዩክሬን ዋና ከተማ ሊገናኙ ነው።
ዜለንስኪ፣ ረጀብ ጣይብ ኤርዶጋን እና አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በዚህ ሳምንት በኪቭ እንደሚገናኙ ተመድ አስታውቋል።
መሪዎቹ ክሬሚያ በሚገኝ የሩሲያ ወታደራዊ ካምፕ ያጋጠመውን ከባድ ፍንዳታ ተከትሎ ነው ወደ ኪቭ የሚያቀኑት።
ሩሲያ 'በሻጥር የሆነ ነው' ባለችው በዚህ ፍንዳታ በመብራት መሠረተ ልማቶች ላይ ውድመት ደርሷል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬንን የሚያስታጥቁትን ምዕራባውያንን በተለይም አሜሪካን ተጠያቂ አድርገዋል።
የፕሬዝዳንት ዜለንስኪ አማካሪ ሚካይሎ ፖዶሊያክ በበኩላቸው ፍንዳታው በሩሲያ ወታደሮች ቁጥጥር ስር ካለው ከዛፓሪዢያ ኒውክሌር ጣቢያ ወደ ክሬሚያ በተዘረጉ የኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ሳያደርስ እንዳልቀረ ተናግረዋል።
ዩክሬን እና ሩሲያ ከሰሞኑ በዛፓሪዢያ ኒውክሌር ጣቢያ ላይ ከደረሱ ጥቃቶች ጋር በተያያዘ እርስበርስ በመወቃቀስ ላይ ነው የሚገኙት። በደቡባዊ ዩክሬን የሚገኘው ኒውክሌር ጣቢያው በዐይነቱ ከአውሮፓ ግዙፉ ነው።
በጣቢያው የሚያጋጥም አደጋ ምናልባትም መላው አውሮፓን ሊያሰጋ እንደሚችል ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ከትናንት በስቲያ ሰኞ ተናግረው ነበር።
ጉዳዩ ዜለንስኪ፣ ኤርዶጋን እና ጉቴሬዝ ነገ ሐሙስ በኪቭ ሲገናኙ ከሚያነሷቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ እንደሚሆንም ተመድ አስታውቋል።