በአዋሽ አካባቢ በተከሰተ የመሬት መንቀጥቀጥ አዲስ አበባ ለ4ኛ ጊዜ የመሬት ንዝረት አጋጠመ
ዛሬ 6 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ላይ ያጋጠመው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 4.7 መሆኑ ተነግሯል
በአዲስ አበባ ትናንት ምሽት 5 ሰዓት ገደማ የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት ለ3ኛ ጊዜ ተሰምቷል
በሬክተር ስኬል 4.6 ሆኖ የተመገዘበ የመሬት መንቀጥቀጥ ዛሬ ጥቅምት 7 2017 ዓ.ም በአዋሽ ፈንታሌ አካባቢ ማጋጠሙ ተነግሯል።
የጀርመን የጂኦሳይንስ የምርምር ማዕከል ባወጣው መረጃ በአዋሽ አካባቢ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 4.7 መሆኑን አስታውቋል።
የመሬት መንቀጥቀጡ ዛሬ እኩለ ቀን 6 ሰዓት ከ10 ደቂቃ አካባቢ ማጋጠሙን እና ለሰከንዶች መቆየቱን ቮልኖ ዲስከቨሪ የጀርመን ጂኦሳይንስ ማእከልን ዋቢ አድርጎ መረጃ አጋርቷል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዚክስና ስፔስ ሳይንስ ዳይሬክተር ዶክተር ኤልያስ ሌዊ በአዲስ አበባ ትናነት ምሽት ከተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ አሁንም መከሰቱን ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አረጋግጠዋል።
ከቀኑ 6 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ከ9 ሰኮንድ በአዋሽ ፈንታሌ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 4.6 አካባቢ እንደሆነም ዶ/ር ኤሊያስ ለኢቢሲ ገልጸዋል።
የመሬት መንቀጥቀጡ የተከሰተው ባለፈው በተከሰተበት አዋሽ ፈንታሌ አካባቢ ሲሆን በአካባቢው ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ እንቅስቃሴ አሁንም እንዳልቆመ ዶ/ር ኤሊያስ ተናግረዋል።
የመሬት መንቀጥቀጡ ንዝረት የት ከተሞች ላይ ተሰምቷል?
የመጀመሪያ ደረጃ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ የመሬት መንቀጥቀጡ ከመሬት በታች 10 ኪሎ ሜትር ጥልቀት ላይ የተከሰተ ብሏል ቮልኖ ዲስከቨሪ።
የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት ክስተቱ ካጋጠመበት ስፍራ አንስቶ እስከ 313 ኪሎ ምትር ርቀት ላይ ከመጠነኛ እስከ ደካማ ንዝረት አሰምቷል።
በመተሃራ እና በአዋሽ ከተሞች ላይ የመሬት መንቀጥቀጡ መካከለኛ የተባለ ንዝረት እንደነበረውም ነው የተገለጸው።
በአዲስ አበባም አነስተኛ ንዝረት የተሰማ ሲሆን፤ በተጨማሪም በገልምሶ፣ በዴሳ፣ አዳማ፣ ወንጂ እና ደብረ ብህሃን ከተሞችን ጨምሮ አደጋው ከተከሰተብት እስከ 313 ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ ባሉ አካባቢዎች ንዝረት ተሰምቷል።