ኤሪክ ቴንሀግ የሚሰናበቱ ከሆነ ቶማስ ቱህል የዩናይትድ ደጋፊዎች ቀዳሚ ምርጫ እንደሆኑ ተነገረ
ቫኒስትሮይ ፣ ጋሬዝ ሳውዝጌት እና እና ዚነዲን ዚዳን ከቡድኑ ጋር ስማቸው ተያይዞ እየተነሳ ነው
በእንግሊዝ ፕርሚየር ሊግ ከአምስት ጨዋታዎች አንድ ጨዋታ ብቻ ማሸነፍ የቻለው የዩናይትድ አሰልጣኝ በከፍተኛ ጫና ውስጥ ይገኛሉ
ባለፉት አስርተ አመታት ውስጥ በእንግሊዝ ፕርሚየርሊግ ፣ በአውሮፓ ሊግ እና ሻምፒዮንስ ሊግ ተፎካካሪ እንዲሁም የሊጎቹም ዋንጫ ባለቤት በመሆን ጠንካራ ክለብ መሆኑን ያስመሰከረው ዩናይትድ ውጤት ከራቀው አመታት ተቆጠሩ።
የቡድኑ የምንግዜም ምርጥ አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን መልቀቀን ተከትሎ በ11 አመት ውስጥ 6 አሰልጣኞችን እና ሁለት ጊዜያዊ አስልጣኖችን የቀያየረው ዩናይትድ የሚፈልገውን ወጥ አቋም እና ውጤት ማስመዝገብ አልቻለም።
ከ2022 ጀምሮ ቡድኑን በአሰልጣኝነት እየመሩ የሚገኙት ኔዘርላንዳዊው አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ ለአመታት በቀጠለው የውጤት መጥፋት ውስጥ ቡድኑን እየመሩ ቀጥለዋል።
ባሳለፍነው አመት በታሪኩ መጥፎ የሚባለውን ጊዜ ያሳለፈው ዩናይትድ በዘንድሮው አመትም በታሪኩ መጥፎ በሚባል የሊግ ጅማሮ እየተወዳደረ እንደሚገኝ እየተነገረ ይገኛል።
በሊጉ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች አንድ አሸንፎ ፣ በሁለት አቻ እና በሁለት ሽንፈት በ14ተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ባሳለፍነው ሰኞ እና ማክሰኞ ሰር ጂም ራትክሊፍ ፣ የቡድኑ ዋና ስራአስፈጻሚ ኦማር ቢራዳ ፣ ዴቬድ ባርይለስፎርድ እና ሌሎችም የቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች በቡድኑ ቀጣይ ሁኔታ እና በአሰልጣኙ እጣፈንታ ዙርያ መረር ያለ ስብሰባ ስለማከሄዳቸው ተሰምቷል።
ስብሰባው የተካሄደው እሁድ እለት በአስቶንቪላ ሜዳ ዩናይትድ ያለምንም ግብ በአቻ ውጤት ከተለያየ በኋላ ነው።
ይህን ተከትሎም የቴንሀግ በዩናይትድ ቤት መቆየት እጅግ እየተመናመነ እንደሚገኝ የእንግሊዝ ጋዜጦች በመዘገብ ላይ ናቸው።
በዚህም ቀጣይ የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ማን ሊሆን እንደሚችል ጋዜጦቹ የተለያዩ ታዋቂ አሰልጣኞችን ከቡድኑ ጋር እያያዙ እየጻፉ ይገኛሉ።
ከዚህ ውስጥ የቀድሞ የቼልሲ አለቃ ቶማስ ቱህል ማንችስተርን ሊረከቡ እንደሚችሉ ሰፊ ግምት ካገኙት መካከል ይጠቀሳሉ።
የቴን ሀግ ምክትል የቀድሞው የቡድኑ ተጫዋች ሩድ ቫንስቲሮይ ቡድኑን በጊዚያዊነት ሊያስለጥን እንደሚችል ሲነገር፤ የቀድሞው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጋሬዝ ሳውዝጌት እና ዚነዲን ዚዳንም ስማቸው ከማንችስተር ዩናይትድ አስልጣኝነት ጋር ተያይዞ እየተነሳ ነው።
የእንግሊዙ ማንችሰተር ኢቪኒንግ ጋዜጣ ቀጣዩ የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ማን ቢሆን ትመርጣላችሁ በሚል ከቡድኑ ደጋፊዎች ድምጽ አሰባስቦ ነበር።
በዚህም ደጋፊዎች ለ9 የተለያዩ አሰልጣኞች ድምጻቸውን የሰጡ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ቶማስ ቱህል 29 በመቶ ድጋፍ በማግኝት ቀዳሚው ሁነዋል።
16 በመቶ ድምጽ በማግኝት ሁለተኛውን ከፍተኛ ድጋፍ ያገኝው የቀድሞው የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ ዚነዲን ዚዳን ነው።
ቫኒስትሮይ ፣ ማስሚላኖ አሌግሪ ፣ ሲሞን ኢንዛጊ ፣ ፣ ማይክል ካሪክ ፣ ግርሀም ፖተር እና ጋሬዝ ሳውዝጌት በተከታታይ ቀጣይ የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ቢሆኑ በሚል ከፍተኛ ድጋፍ ያገኙ ናቸው።