ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር ተያያዝ በቁጥጥር ከዋሉት ውስጥ ይቅርታ የጠየቁ በርካታ ሰዎች እንዲለቀቁ ተደርጓል- መንግስት
ከህወሓት ነፃ በውጡ የአማራና አፋር ክልል የተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎችና አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ ነው
መከላከያ ወደ ትግራይ እንዳይገባ የተደረገው የትግራይ ሕዝብ በድጋሚ የማስተዋል ጊዜ እንዲያገኝ በማሰብ መሆኑን አስታውቋል
ከአስቸኳይ ጊዜ አወጅ ጋር ተያያዝ በቁጥጥር ከዋሉት ውስጥ ጥፋታቸውን አምነው ይቅርታ የጠየቁ በርካታ ሰዎች እንዲለቀቁ መደረጉን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በዛሬው እለት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በመግለጫቸው፤ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ በሽበር ከተፈረጁ ቡድኖች ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል በርካታ የተጠረጠሩ ግለሰቦች በፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ውለው እንደሚገኙ አስታውሰዋል።
ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉ ግለሰቦች ውስጥም ከሽበር ቡድኖች ጋር አብሮ መስራታቸው ሀገርን እንደመካድ የሚቆጠር መሆኑን አምነው እና በድርጊታቸው ተጸጽተው ይቅርታ የጠየቁ፤ የጥፋት ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆነ እና መንግስት ከጥፋታቸው ተገቢውን ትምህርት ወስደዋል ብሎ ያመነባቸውን በርካታ ሰዎች በይቅርታ እንዲለቀቁ ማድረጉን ገልፀዋል።
በእስር ላይ የነበሩ ግለሰቦችን መልቀቁ እስከ ትናት ቀጥሎ መካሄዱን ያስታወቁት ዶ/ር ለገሰ፤ በቀጣይም የጥፋት ደረጃቸው እየተታየ የሚለቀቁ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም አስታውቀዋል።
ዶ/ር ለገሰ በመግለጫቸው አክለውም በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአማራ እና በአፋር ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች በህወሓት ኃይል የተወረሩ አካባዎችን ነፃ በማውጣት መጀመሪያውን ምእራፍ በማሳካት የያዘባቸው አካባቢዎችን አጽንቶ እንዲቆይ በመንግስት መታዘዙን አስታውሰዋል።
መከላከያ ሰራዊቱ በያዘባቸው ቦታዎች እንዲቆይ ከታዘዘ ጊዜ ጀምሮ ምንም አይነት እንቅስቃሴ አለማድረጉንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
“መንግስት የመከላከያ ሰራዊት ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገባ የወሰነው የትግራይ ህዝብ በመጀመሪያው ዙር የህግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት ያባከነውን የማስተዋያ ጊዜ ዳግም እንዲያጤን እና ራሱን ከአሸባሪ ኃይል በመነጠል ለጥቅሞቹ እና መብቶች እንዲቆም ተጨማሪ እድል ለመስጠት በማሰብ ነው” ብለዋል።
“በአሁኑ ወቅት የትግራይ ህዝብ በርካታ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያው ችግሮች እንዳሉበት መንግስት ይገነዘባል” ያሉት ዶ/ር ለገሰ፤ትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያ አንዱ አካል በመሆኑ መንግስት ችግሮቹ እንዲፈቱለት የበኩሉን ድርሻለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።
“የትግራይ ህዝብ ያሉበት የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያው ችግሮች እንዲፈቱለት ከፈለገ በጦርነት ብቻ የመኖር ፍላጎትና ጥማት ያለውን የህወሓት ቡድን ዳግም የትግራይን ህጻናት በጦርነት እንዳይማግድ ህዝቡ ማስቆም አለበት” ብለዋል።
በሀገር ውስጥም ይሁን በውጪ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ትግራይ ክልል እና ህዝብ ወደ ቀደመ ሰላማዊ እንቅስቃሴው እንዲመለስ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል ህወሓት በከፈተው ጦርነት የተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎችና አካባቢዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አክለው አስታውቀዋል።
መላው ኢትዮጵያዊ ለመልሶ ማቋቋሙ ድጋፍ እንዲያደርግ የጠየቁት ሚኒስትሩ የቴሌኮም፣ የኤሌትሪክ፣ የባንክ እና መሰል አገልግሎቶች ወደ ሥራ መመለሳቸውን ተናግረዋል።