በርካታ አለማቀፍ ተቋማት አገልግሎታቸው ታወከ
የአሜሪካና አውስትራሊያ ባንኮች፣ አየርመንገዶች እና ሚዲያዎች አገልግሎታቸውን መስጠት ተቸግረዋል ተብሏል
ችግሩ የተፈጠረው የማይክሮሶፍት 365 መተግበሪያዎችን በሚጠቀሙ ኮምፒውተሮች ላይ መሆኑ ተገልጿል
በርካታ አለማቀፍ ተቋማት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስርአታቸው ላይ በተፈጠረ ችግር አገልግሎታቸው መታወኩ ተነገረ።
ከዛሬ ማለዳ ጀምሮ የተከሰተው ችግር ባንኮች፣ አየርመንገዶች እና የሚዲያ ተቋማትን ስራ ማስተጓጎሉም ተገልጿል።
አውስትራሊያ በተለይ ከፍተኛ የአገልግሎት መቋረጥ የተከሰተባት ሀገር ሆናለች።
በሀገሪቱ በረራዎችን ማካሄድና በሱፐርማርኬቶች ግብይት ለመፈጸም አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሯል የተባለ ሲሆን፥ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችም ስርጭታቸው በአግባቡ ማስተላለፍ ተስኗቸዋል ተብሏል።
የበርካታ ተቋማት ኮምፒውተሮች ስራ ማቆማቸውንም ነው ቢቢሲ የዘገበው።
በሲድኒ አውሮፕላን ማረፊያ ለመንገደኞች የበረራ ጥቆማ የሚሰጡ ኮምፒውተሮች ስራ ማቆማቸውንና እንደ ቨርጂል አውስትራሊያ ያሉ አየርመንገዶች በረራ ለጊዜው ማቋረጣቸውን ይፋ ማድረጋቸውም ተዘግቧል።
የአውስትራሊያ ባንክ፣ የቴሌኮም ኩባንያው ቴልስትራ እና ሌሎች ተቋማትም አገልግሎት መስጠት እንደተቸገሩ ዳውን ዲቴክተር አስነብቧል።
በአሜሪካም የአላስካ ግዛት የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት መስጫ መስመሩ (911) በሚገባ እየሰራ አለመሆኑን አስታውቋል።
የለንደን የአክሲዮን ገበያ በአውስትራሊያ እና አሜሪካ ያጋጠመው አይነት ችግር እንደገጠመው የተገለጸ ሲሆን፥ በርካታ ሀገራትን ያዳርሳል ተብሎ የሚጠበቀው ችግር መንስኤ እስካሁን በግልጽ አልታወቀም።
አብዛኞቹ ችግሩ የገጠማቸው ተቋማት የማይክሮሶፍት 365 መተግበሪያዎችን ይጠቀማሉ መባሉን ተከትሎ ከዚሁ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ሬውተርስ ዘግቧል።
የአውስትራሊያ የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር ግን የአገልግሎት መታወኩ የገጠመው “ክራውድስትራይክ” ከተባለው አለማቀፍ የሳይበር ደህንነት ተቋም ጋር በተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል።
ይሁን እንጂ በአውስትራሊያ፣ አሜሪካ እና ብሪታንያ የገጠመው ችግር ከሳይበር ጥቃት ጋር የተያያዘ ይሆናል ብሎ እንደማያምን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
የስፔን፣ ጀርመን ፣ ስኮትላንድ፣ ሆላንድ እና ሎሎች የአውሮፓ ሀገራት አውሮፕላን ማረፊያዎችም ተመሳሳይ ችግር እንደገጠማቸው ሪፖርት አድርገዋል።
የብሪታንያው ስካይ ኒውስም በገጠመው ችግር ስርጭት ለማቋረጥ መገደዱን ነው ያስታወቀው።